በፌደራል አስተዳደር ስነ ስርዐት አዋጅ በፍርድ ቤት የሚሰጡ የውሳኔ ክለሳ ስነ-ስርዐት የዳሰሳ ጥናት ላይ የቫሊዴሽን ወርክሾፕ ተካሄደ

Validation Workshop Held on a Survey of Judicial Review Procedures under the Federal Administrative Procedure Proclamation

የፌደራል አስተዳደር ስነ -ስርዐት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 ቁልፍ በሆነ የሕግ አተገባበር ክፍተቶች ላይ ተመስርቶ የክለሳ ስነ- ስርዐት የዳሰሳ ጥናት በፍርድ ቤቶች በሚል በፍትሕ ሚኒስቴር የፌደራል ህጎች ተፈፃሚነት ዳይሬክቶሬት አማካኝነት በተጠና ጥናት ላይ የቫሊዴሽን ወርክሾፕ ዳኞች፣ጠበቆች እና ሌሎች የጥናቱ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ሃያት ሪጀንሲ ሆቴል ተካሂዷል።

በዚህ ወቅት የአስተዳደር ስነ -ስርዐት አዋጁ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመፍታት አስተዳደራዊ ፍትሕን በማስፈን በኩል ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን የገለፁት በፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ኤርሚያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) አዋጁ የህብረተሰቡን የእለት ተእለት የፍትሕ ጥያቄን በመመለስ ፍትሕን ለማስፈን የወጣ አዋጅ መሆኑንም አክለዋል።

በመሆኑም የዚህን አዋጅ አተገባበር በተመለከተ ተቋሙ በሕግ በተሰጠው ኃላፊነት ተመስርቶ የዳሰሳ ጥናቶች እያደረገ እንደሚገኝ ገልፀው የዛሬው በፍርድ ቤቶች ላይ የተካሄደው የክለሳ ስነ -ሥርዓት የዳሰሳ ጥናት በዋናነት ክለሳ ሲካሄድ አዋጁ ላይ በተቀመጠው አግባብ ውሳኔ እየተሰጠ ነው ወይ? የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ መነሻ አድርጎ የተሰራ መሆኑንና በግኝቱ ተመስርቶ ክፍተቶችን በጋራ በማየት ለማስተካከልና ጥሩ የሆኑ ልምምዶችን ደግሞ አጠናክሮ ለማስቀጠል ታስቦ ጥናቱ ለውይይት መቅረቡን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ የአስተዳደር ስነ-ስርዐት አዋጅ የክለሳ ስነ -ስርዐት የዳሰሳ ጥናት ተካሂዶ ውይይት እንደተካሄደበት የገለፁት በፍትሕ ሚኒስቴር የፌደራል ህጓች ተፈፃሚነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሐወኒ ታደሰ ዛሬ ለውይይት የቀረበው የክለሳ ጥናትም ሁለተኛውና ከ2013 ዓ.ም እስከ 2016 ዓ.ም ባሉ አመታት በአስተዳደር ስነ ሥርዓት ችሎት የታዩ መዛግብት የተዳሰሱበት መሆኑን ተናግረዋል።

ጥናቱ አስተዳደር ስነ ስርዐት አዋጁ የሚተረጎምበት እና ስራ ላይ የሚውልበትን መንገድ በመዳሰስ የሕግ አተገባበር ተግዳሮቶችን በመለየት የመፍትሄ ሀሳብ መጠቆምን ዓላማው አድርጎ የተሰራ ሲሆን በአስተዳደር ስነ -ሥርዓት ችሎት የታዩ 185 መዛግብትን በመዳሰስና ችሎት ከተሰየሙ ዳኞች እና ሌሎች የሕግ ባለሙያዎች ቃለ መጠይቅ በማድረግ መሰራቱ ተጠቁሟል።

በአስተዳደር ተቋማት ከሚሰጡ አገልግሎቶች፣ ከመመሪያ እና ከአስተዳደር ውሳኔ ጋር በተያያዘ በሚፈጠሩ ቅሬታዎች ዜጎች ጉዳያቸውን ወደ አስተዳደር ችሎት የሚወስዱ ሲሆን አዋጁ ስራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በአስተዳደር ችሎት በታዩ የውሳኔ ክለሳ ግኝቶች ውስጥ ከመመሪያ ጋር በተያያዘ ከሥልጣን ገደብ ውጭ እና ስነ ሥርዓት ሳይከተሉ የሚወጡ መመሪያዎች ለአብነት ተጠቃሽ ሲሆኑ ከአስተዳደር ውሳኔ ጋር በተገናኘ ደግሞ የመደመጥ መርህን መጣስ ፣በተገቢው ጊዜ አለመወሰንና ከቅን ልቦና ውጭ የተሰጡ ውሳኔዎች የሚሉና ሌሎች ግኝቶች ሲጠቀሱ በግኝቶቹ እና የመፍትሄ ሃሳቦች ላይ ከውይይቱ ተሳታፊዎች በኩል ጥያቄ እና ሰፋ ያሉ አስተያየተቶች ቀርበው ምላሽና ማጠቃለያ ተሰጥቶባቸዋል።

Tagged Under: 1183/2012 • administrative • administrative courts • administrative justice • case studies • court • court decisions • decisions • federal • Federal Administrative Procedure Proclamation • Good Governance • judicial • judicial review • Justice • legal • Legal Compliance • Legal Reform • no. • Policy Implementation • procedure • proclamation • proclamation no. 1183/2012 • reform • regulatory compliance • review • Stakeholder Consultation • survey • validation • workshop
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች