በኢትዮጵያ ውስጥ በፌደራል ደረጃ ባሉ የአስተዳደር ፍርድ ቤቶች የሕግ ማዕቀፍ አደረጃትና አሠራር ላይ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ዙሪያ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ በውይይት መድረኩ እንደገለፁት በአስተዳደር ፍርድ ቤቶች የነበሩ ክፍተቶችን ለማስተካከል እየተሰራ ቢሆንም፣ ነገር ግን አሁንም ከሌሎች አበረታች የሆነ የአስተዳደር ፍርድ ቤቶች ሕግ ካላቸው የአፍሪካ ሀገራት አንፃር መስተካከል የሚገባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ጠቅሰው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ የአስተዳደር ፍርድ ቤቶች መዋቅርና አደረጃጀት ላይ መሠረታዊ የሆነ ለውጥን ለማምጣት ወጥ የሆነ ቅርፅ እና አደረጃጀት እንዲኖራቸው ለማስቻል በጉዳዩ ላይ መምከርና ግብዓት ማሰባሰብ ከባለድርሻ አካላት የሚጠበቅ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በመድረኩ በ3 አመቱ የትራንስፎርሜሽ እቅድ ትግበራ ማዕቀፍ ውስጥ ተካቶ የተዘጋጀ መሆኑ የተመለከተው የዳሰሳ ጥናት ቀርቦ ገለፃ ተደርጎበታል፡፡ በጥናቱም የአስተዳደር ፍርድ ቤቶች የሕግ ማዕቀፍ፣ የአደረጃጀት እንዲሁም አሠራር ላይ አጠቃላይ ዳሰሳ የተደረገበት መሆኑ የተመላከተ ሲሆን በፌደራል ደረጃ የሚገኙ የአስተዳደር ፍርድ ቤቶችን አስተዳደርና አደረጃጀት ችግሮችን ለመለየት እንደሚያግዝ ተመልክቷል፡፡
በዘርፉ ላይ ጥሩ አፈፃፀም ያላቸውን ሀገራትን ልምድ ተመልክቶ የተዘጋጀው ይህ ጥናት፤ የአስተዳደር ፍርድ ቤቶች ፈጣን ፍርድ በመስጠት እንዲሁም የመደበኛ ፍርድ ቤቶችን ጫና መቀነስ የሚያስችሉ፤ ተደራሽ እና ወጪ ቆጣቢ መሆናቸው፤ ልዩ እውቀት ያላቸው ዳኞች ስለሚገኙባቸው ጠቀሜታቸው ከፍ ያለ መሆኑ፤ በሌላም በኩል በአስፈጻሚው አካል ስር የሚገኙ መሆናቸው ነጻነትታቸው ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩ፣ ወጥ የሆነ የአደረጃጃት እና የሚመሩበት ስነ-ስርዐት ካለመኖሩ፣ የሚሰጡት ውሳኔ ላይ የተፃሚነት ወስንነት እና በተጨማሪም በቂ የሰው ኃይልና አለመኖር የጥናቱ ግኝቶች ተብለው የተለዩ ጉዳዮች መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን የአስተዳደር ፍርድ ቤቶችን የሚመለከት ወጥ የሥነ ሥርዓት ሕግ ቢኖር፤ ዓለም ዓቀፍ አደረጃጀቶችን ያማከሉ ገለልተኛ እና ነጻነት ያላቸው ተደራሽ መሆን የሚችሉበት አሠራር ቢዘረጋ የሚሉና ሌሎች ጉዳዮች በዳሰሳ ጥናቱ ውስጥ በምክረ ሀሳብነት ተይዘው ለውይይት ቀርበዋል፡፡
በተደረገው ውይይት ላይ ለተነሱት ሀሳቦች የማጠቃለያ ምላሽ የሰጡት በፍትሕ ሚኒስቴር የፌደራል ህጎች መከታተያ ዳሬክቶሬት ዳሬክተር ወ/ሪት ሀወኒ ታደሰ መድረኩ የዳሰሳ ጥናቱ ያላካተታቸውን ጉዳዮች ለማየት ያስቻለና በቀጣይነት ያሉትን የአስተዳደር ፍርድ ቤቶች ጉዳይ ከመደበኛ ችሎት ጋር የተወራረሱ ጉዳዮች ካሉ እነሱን ለይቶ ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው፤ የተሻለ አፈፃፀም ያላቸው ሀገራትን ልምድና ተሞክሮ ማየት አስፈላጊ መሆኑንና በቀጣይም የሚከናወኑ ተግባራትን ባለድርሻ አካላት አስቀድሞ እንዲያውቁ ያደረግ መድረክ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ፣ ከሲቪል ሰርቪስ፣ ከግብር ይባኝ ኮሚሽን፣ ከንግድ ውድድርና ሸማቶች ጥበቃ አስተዳዳረዋ ፍርድ ቤቶችና ችሎቶች እንዲሁም ከፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና ከፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተወከሉ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡