የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ እንዲሁም የድሬደዋ እና የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በ2017 በጀት ዓመት 12 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና የህብረተሰቡን ጥቅሞች ለማስከበር ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል አንዱ በሆነው የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የወንጀል ምርመራ፣ ክስና ክርክሮችን በማድረግ ፍትሕን ለማስፈን ከሚከናወኑ ስራዎች መካከል በ2017 በጀት ዓመት 12 ወራት ተከናወኑ ተግባራት የሚመለከታቸው የቅርንጫፍ ጽ/ቤት የስራ ኃላፊዎችና የቡድን መሪዎች በተገኙበት የእቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡
የውይይት መድረኩን የመሩት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች መከታተያ ዳሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ ጌቱ ታደሰ ባደረጉት ገለፃ በበጀት አመቱ የወንጀል ፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥ አቅምንና ተደራሽነትን ለማሳደግ፤ ምርመራቸው ተጠናቀው ለቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ለውሳኔ ቀርበው መወሰን ካለባቸው 52,908 የምርመራ መዝገቦች ውስጥ 97% በሚሆኑ መዛግብት ላይ ውሳኔ ለመስጠት ታቅዶ በ52,627 ወይም (99.5%) መዝገቦች ላይ ውሳኔ መስጠት መቻሉና ይህም ከባለፈው ዓመት አንፃር 4,057 መዛግብት ዐቃቤ ሕግ ጭማሪ ውሳኔ የሰጠባቸው መሆኑንና የውዝፍ ምጣኔውንም ከ1.4% ወደ 0.5% ማውረድ እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡
በሪፖርቱ በኢኮኖሚ፣ በሙስና፣ በተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ፣ በልዩ ልዩ ወንጀሎች እንዲሁም በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች የምርመራ መዛግብት ላይ ውሳኔ በመስጠት ከማጥራት አኳያ የማጥራት ምጣኔ አፈፃፀማቸው ከተያዘው እቅድ አንፃር መልካም አፈፃፀም የተመዘገበባቸው እንደሆነ ማወቅ ተችሏል፡፡ ከዚህም አንፃር በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ያለውን የሠው ኃይል እጥረት ሸፍኖ በርካታ መዛገብት ላይ ዐቃቤ ሕግ ውሳኔ እንዲሰጥበት በማድረግ መልካም አፈፃፀም ማስመዝገብ መቻሉ እንደ ጥንካሬ የሚጠቀስ መሆኑን ተጠቁሟል፡፡
የሰብዓዊ መብትን የማክበር አፈፃፀምን በሚመለከት በ12 ወራት ውስጥ፤ በአጠቃላይ 26‚142 ተጠርጣሪዎችን በማረሚያ ቤት ተገኝቶ በመጎብኘት የታዩ ችግሮች ተለይተው መፍትሔ እንዲሰጣቸው ለማድረግ የተቻለ መሆኑ ተነስቷል፡፡ በተያያዘም በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች አማካኝነት አዲስ አበባን ጨምሮ ድሬደዋ እና ሀዋሳ ላይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅመዋል በተባሉ የፖሊስ አባላት ላይ ክስ ቀርቦባቸው በክርክር ላይ የሚገኙ እና ምርመራ የተጀመረባቸው መሆኑ ታውቋል፡፡
በመጨረሻም በቀረበው ሪፖርት ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎ፣ በፍትሕ ሚኒስቴር በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች መከታተያ ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጌቱ ታደሰ ባስተላለፉት መልዕክት ሁሉም አካላት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ በማሳስብ ቀጣይ የስራ አቅጣጫዎችን ካመላከቱ በኋላ የእቅድ አፈፃፀም የውይይት መድረኩ ተጠናቋል፡፡