የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ከUnited Nations Development Programme እና Hague Institute for Innovation of Law ጋር በመተባበር በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሰሜን ሸዋ ዞን ልዩ ስሙ በልቼ ቀበሌ ሥራ ለጀመረው ሞዴል ባህል ፍርድ ቤት የቢሮ ዕቃዎች እና ለሽማግሌዎች የአቅም ግንባታ የሥልጠና ወጪ ድጋፍ አደረገ።
በሞዴል የባህል ፍርድ ቤቱ የሥራ ማስጀመሪያ እና ለሽማግሌዎች የአቅም ግንባታ ሥልጠና ፕሮግራም ላይ የፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርሚያስ የማነብርሃንን ጨምሮ የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፣ የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳዳሪ፣ የደብረብርሃን ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ እንዲሁም ሌሎች የፌዴራልና የክልል አመራሮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት እና ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።
በመድረኩ እንደተመላከተው ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች ለዘመናት በሀገራችን ውስጥ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታትና ማህበራዊ አንድነትን በማጠናከር ከፍተኛ ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል። በተለያዩ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ጥናቶችም እነዚህ ሥርዓቶች በማህበረሰቡ ዘንድ ሰፊ ተቀባይነትና ታአማኒነት እንዳላቸው መረጋገጡ ተጠቅሷል።
በዚህ መነሻነትም መንግሥት ለባህላዊ ፍትሕ ሥርዓቶች ትኩረት በመስጠት የሕግ ማዕቀፎችን እና ተቋማዊ ድጋፎችን እያጠናከረ መሆኑ ተገልጿል። እየተገባደደ በሚገኘው በሦስት አመቱ የፍትሕ ትራንሰፎርሜሽን ታቅደው ሲተገበሩ ከቆዩት አስሩ አምዶች ውስጥ አንዱ እና ውጤት እያስገኘ የሚገኘው የመሠረተ ማኅበረሰብ ፍትሕ አገልግሎት አንዱ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም የአማራ ክልልን ጨምሮ ዘጠኝ ክልሎች ለባህላዊ ፍትሕ ሥርዓቶች የሕግ እውቅና መስጠት መቻላቸው ተጠቁሟል።
የባሕል ፍርድ ቤቶች ፍትሕን ወደ ሕዝቡ በማቅረብ፣ ወጪና ጊዜን በመቆጠብ፣ ቀላልና ለማህበረሰቡ የተለመደ ሂደት በመከተል የእውነት ፍለጋን እና የተበላሹ ማህበራዊ ግንኙነቶችን መጠገን የሚያስችሉ ውጤታማ የፍትሕ ሥርዓቶች መሆናቸው እና ከግጭት መፍታት ባለፈም ዘላቂ ሰላምንና ማህበራዊ መተሳሰብን በማጠናከር ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተወስቷል።
በአማራ ክልል በ1,170 ቀበሌዎች የባህል ፍርድ ቤት ዳኞች ምርጫ መካሄዱ የተገለጸ ሲሆን፣ ሴቶች በግጭት አፈታትና በማህበራዊ እርቅ ሂደቶች ያላቸውን ጉልህ ሚና በማገናዘብ ከ400 በላይ ሴት ሽማግሌዎች መመረጣቸውም ተጠቅሷል። በሰሜን ሸዋ ዞን ብቻ በ94 ቀበሌዎች 470 ሽማግሌዎች የተመረጡ ሲሆን፣ በ20 ቀበሌዎች የማስቻያ ቦታዎች መዘጋጀታቸው ተገልጿል።
በፕሮግራሙ መጨረሻም ለተመረጡ ሽማግሌዎች የሰብዓዊ መብት አጠባበቅ ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ ሰሥልጠና በይፋ የተጀመረ ሲሆን፣ ይህ ተነሳሽነት ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶችን በማጠናከር ፍትሕን ለማህበረሰቡ ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ እና በማህበረሰብ ደረጃ የሚከሰቱ ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተመላክቷል።