ሀገር አቀፍ የተቀናጀ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂ ላይ ለፌደራል ፖሊስ አመራሮች እና አባላት ስልጠና እየተሰጠ ነው

Training on National Integrated Crime Prevention Strategy Provided to Federal Police Leaders and Members

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ ሕግ ትምህርት እና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ለፌደራል ፖሊስ አመራሮች እና አባላት በሀገር አቀፍ የተቀናጀ የወንጀል መከላከል ስትራቴጂ እና ሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ሥልጠና በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡

ሥልጠናውን በንግግር የከፈቱት በፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታ እና ሪፎርም ዘርፍ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ መዝሙር ያሬድ ከፌደራል ፖሊስ ጋር ያለን ቅንጅታዊ አሠራር የተጠናከረ ነው ያሉ ሲሆን ወንጀልን መከላከል በቀዳሚነት የፌደራል ፖሊስ ተግባር መሆኑን እና ፌደራል ፖሊስ የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም ብዙ ስኬቶች ማስመዝገቡን ገልጸዋል፡፡ አክለውም ወንጀል መከላከል የቅንጅት ስራን የሚጠይቅ በመሆኑ የፍትሕ አካላት እና ተቋማት ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት መሥራት እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ዋና ጠቅላይ መምሪያ ጽ/ቤት ምክትል ዋና መምሪያ ኃላፊ ክቡር ረዳት ኮሚሽነር ሞገስ ቸኮል በበኩላቸው ፌደራል ፖሊስ በመላ ሀገሪቱ የወንጀል መከላከል ስራዎችን እየሰራ መሆኑን አውስተው በሀገር ላይ የሚቃጡ ጥቃቶችን በመከላከል ደረጃ የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር አኩሪ የሆኑ ተግባሮችን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡ አያይዘውም ይህንን ስንሰራ በእውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን የወንጀል መከላከል ስትራቴጂያችን ምንድነው? ፣ ምን ላይ ያተኩራል? ፣ ከተልዕኳችን ጋር እንዴት እናጣጥመው? ፣ የሚለውን በተገቢው መንገድ ለመጨበጥ ይህ ሥልጠና ከፍተኛ አስተዋፅኦ አለው ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ሁሉም ሰልጣኞች በዚህ ሥልጠና የሚያገኙትን እውቀት በየክፍላቸው እና አባሎቻቸው በማጋራት እና ተግባራዊ በማድረግ ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት መሥራት እንደሚገባቸውም ኮሚሽነሩ አመላክተዋል፡፡

ሥልጠናውን በፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ ሕግ ትምህርት እና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ዐቃብያነ ሕግ የሆኑት አቶ መስፍን መኮንን እና አቶ ተሰማ ግደይ የሰጡ ሲሆን ሥልጠናው ከሚያዝያ 15 ቀን 2ዐ16 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ 3 ቀናት የሚሰጥ መሆኑን እና በቀጣይም በ3 ዙር በርከት ላሉ የፌደራል ፖሊስ አባላት እንደሚሰጥ ተመልክቷል፡፡

Tagged Under: Capacity Building civil liberties Crime crime prevention strategy criminal justice reform Education federal Federal police fundamental rights human Human Rights integrated integrated crime prevention Justice Justice Ministry law law enforcement training learning Legal Training ministry National Strategy Police police reform prevention Rights Rule of Law skill development Strategy Training
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች