የብሔራዊ ትብብር ጥምረት የፌደራልና የክልል የሕግ ማስከበር የሥራ ቡድን ዓመታዊ ሪፖርት ግምገማ በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ሲሆን ስብሰባው በቅርቡ በየመን በደረሰ የጀልባ አደጋ ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች የህሊና ጸሎት በማድረግ ተጀምሯል።
መደበኛ ባልሆነ መንገድ ከአገር ለመውጣት በሚደረገው ሂደት ውስጥ ዜጎቻችን በሰው መነገድ እና ሰውን በሕገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀሎች ሰለባ ከመሆናቸው በተጨማሪ በሀገር ደኅንነትና በፋይናንስ ሥርዓቱ ላይ የተደቀነውን ስጋት እየጨመረ መምጣቱን በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ የተከበሩ አቶ ተስፋዬ ዳባ ተናግረዋል።
አክለውም የወንጀል ቡድኖቹ ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም በርቀት ሆነው ለዜጎች ተጨባጭ ያልሆነ ተስፋ በመስጠት፣በማታለልና በማስገደድ በወንጀል ተግባር ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ ለከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና ቁሳዊ ኪሳራ እየዳረጓቸው እንደሚገኙ ገልፀዋል።
እነዚህን ወንጀሎች በተባበረ ክንድ መታገል ለነገ የማይባል ጉዳይ መሆኑንና በተለይም በመልማዮች፣ በአዘዋዋሪዎችና በድንበር አሻጋሪዎች በተለይም በዋነኞቹ የወንጀል ተዋንያን ላይ የሚወሰደው እርምጃ የተጠናከረ ሊሆን እንደሚገባ የተመላከተ ሲሆን በሌላ በኩል በሀገር ውስጥ በሚፈፀም የሰው መነገድ ወንጀል ምክንያት በተለይም በሴቶችና ሕፃናት የሚፈፀሙ ብዝበዛዎችም ከድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች እኩል ትኩረት የሚሹ መሆናቸውም ተጠቁሟል።
አገራችን ወንጀሎቹን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሕግ፣የአደረጃጀትና የአሠራር ሥርዓቶችን በማጠናከር የበርካታ ተቋማትን ትብብርና ቅንጅት የሚፈልግ መሆኑን በመረዳት ትኩረት ሰጥታ እየሰራች እንደምትገኝና ከችግሩ ስፋት አንፃር መሰራት ያለባቸው በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም ተቋማዊ የትብብር አደረጃጀቶቹ ከተዘረጉ በኋላ ተቋማቱ ሲያካሂዱት የነበረውን ተናጥላዊ የምላሽ አሰጣጥ ወደ ቅንጅት በማምጣት የጋራ ማዕቀፍ በማሰባሰብ ረገድ መልካም ጅምሮች መታየታቸው ተገልጿል።
በዚህም በ2017 የበጀት ዓመት በሰው የመነገድ እና ሰውን በሕገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀል ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተለይም በወንጀል ምርመራና ክርክር በአገርዓቀፍ ደረጃ የተጠናከረ ሥራ ለመሥራት የተሞከረበት ዓመት መሆኑንና በእነዚህ ወንጀሎች በተሳተፉ ወንጀለኞች ላይ ከ25 ዓመት ጽኑ እስራት እስከ የእድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ መደረጉም ለአብነት ተነስቷል።
በተጨማሪም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተለይም ዐቃቤ ሕግ፣ ፓሊስና የደኅንነት ተቋማት በጥብቅ ቅንጅት በመሥራት ስትራቴጂካዊ የወንጀል ምርመራ በማምጣት በተናበበ መልኩ የሕግ ማስከበሩን ውጤታማ ማድረግ እንደሚገባም ተመላክቷል።
አገራዊ የሕግ ማስከበር ዓመታዊ የግምገማ መድረኩ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን በቆይታው የሕግ ማስከበር የሥራ ቡድኑ የፌደራልና የክልል ሪፖርት፣ ከወንጀል ምርመራ ጋር በተያያዘ ያጋጠሙ ችግሮችና በቀጣይ የሚሰሩ ዋና ዋና ተግባራት፣ የምርመራ ስራዎች፣ የተጎጂዎች ጥበቃ መልሶ ማቋቋም እና መሰል ጉዳዮች ቀርበው ውይይት የሚደረግበት ይሆናል።
መድረኩን የፍትሕ ሚኒስቴር ከዓለምዓቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) እና አጋር ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር አዘጋጅተውታል።