በፍትሕ ሚኒስቴር የፌደራል ሕጎች ተፈፃሚነት መከታተያ ዳይሬክቶሬት በምግብና መድኃኒት ደኅንነትና አስተዳደር ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1112/2010 አስመልክቶ ባደረገው ክትትል በተሰጠ የምክረ-ሀሳብ አተገባበር ላይ ያደረገውን የዳግም ክትትል ሪፖርት ባለድርሻ አካላቱ በተገኙበት ውይይት ተካሂዶበታል።
በውይይቱ የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ እያሱ ቀለሜ ተቋሙ በአዋጅ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ሕጎች ተግባራዊ መደረጋቸውንና አስፈፃሚ የፌደራል መንግሥት ተቋማት በሕጉ መሠረት ስራቸውን እያከናወኑ እንዲሁም የመከታተልና የማረጋገጥ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገልፀዋል።
ክትትል ከተደረገባቸው ተቋማት መካከልም የምግብና መድኃኒት ደኅንነትና አስተዳደር ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1112/2010 አስመልክቶ ከዚህ ቀደም በ2013 ዓ.ም በተደረገ ክትትል እና ግኝቶች ተመስርቶ በወቅቱ የተሰጡ ምክረ ሀሳቦች አተገባበርን በተመለከተ በተደረገ ዳግም ክትትል ሪፖርት ላይ ውይይት መደረጉ በክትትሉ የተደረሰባቸውን ግኝቶችንና የነበራቸውን ጥንካሬ የበለጠ ለማዳበር ክፍተቶቹን በቀጣይ ለማስተካከል ዕድል እንደሚፈጥር ገልፀዋል።
የዳግም ክትትል ሪፖርቱ እንዳመላከተው ጥናቱ ከዚህ ቀደም በ2013 በተደረገን ጥናት መሠረት ተሰጥተው ከነበሩ 11 ምክረ ሀሳቦች ውስጥ ተግባራዊ የተደረጉ፣ በከፊል ተግባራዊ የተደረጉ እና ያልተደረጉ በሚል በዳግም ክትትሉ የመለየት ሥራ የተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አክለውም በወቅቱ ተሰጥተው ከነበሩትና ተግባራዊ ከተደረጉት ምክረ ሀሳቦች ውስጥ የምግብ ደኅንነት ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ እንዲፀድቅ መደረጉ፣ የባለድርሻ አካላት ጥምረት የሚመራበት ብሔራዊ ምክር ቤት እንዲቋቋም የፓሊሲ አቅጣጫ መቀመጡ፣ የቁጥጥር ተቋማት በዘመናዊ ላብራቶሪ እንዲደራጁ ማድረግን በተመለከተ በተለይም የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን የላብራቶሪ አቅምን ለማሳደግ የማሽኖች ግዥ መፈፀሙ፣ ደረጃ ያልወጣላቸውን የሕፃናት ምግብ፣ ወተት እና ስጋ አስገዳጅ ደረጃ እንዲወጣ ማድረግን በተመለከተም አስገዳጅ የጥራት ደረጃ የወጣላቸው መሆኑንና እና ሌሎች ምክረ ሀሳቦችን በዝርዝር አንስተዋል።
ሌላው በተሰጠው ምክረ ሀሳብ መሠረት በከፊል ተግባራዊ የተደረጉ ሲሆኑ ለአብነትም የምግብ ደኅንነትና ጥራት ችግር ያስከተለውን የጤና ጉዳት ለማወቅ አገራዊ ጥናት ማድረግ በተመለከተም አሁንም ክፍተቶች እንዳሉ ተነስቷል።
ከተደረገው ዳግም ክትትል ተግባራዊ ያልተደረጉ ምክረ ሀሳቦች በተመለከተም ምግብ ነክ የሆኑ ህጎችን እንደ አገር ወጥ በሆነ መልኩ የሕግ ማዕቀፎች እንዲዘጋጁ ቢመላከትም አሁንም ሕጎች በተናጠል እየወጡ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር በመቀላቀል የተጠረጠሩ ሰዎችን የወንጀል ተጠያቂነት የሕግ ክፍተት ማሻሻልን በተመለከተም እስካሁን የተደረገ ማሻሻያ አለመኖሩ እና ሌሎች ምክረ ሀሳቦች ተነስተዋል።
በውይይቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ኃላፊዎች፣ የሚመለከታቸው የሚኒስቴር እና ባለሥልጣን መስሪያ ቤቶች ተወካዮች ተሳትፈዋል።