በ8ኛው የፍትሕ ሚኒስቴር እና የክልል ፍትሕ ቢሮዎች የጋራ ጉባኤ በድሬዳዋ ከተማ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት ሲካሄድ ቆይቶ በከተማዋ እየተካሄዱ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶችን በመጎብኘት ተጠናቋል፡፡
“የሕግ የበላይነትና ሰብዓዊ ክብርን ያረጋገጠ ፣ተዓማኒ የፍትሕ ሥርዓት እንገነባለን” በሚል መሪ-ቃል በደማቅ ሁኔታ ሲካሄድ የቆየው 8ኛው የፍትሕ ሚኒስቴር እና የክልል ፍትሕ ቢሮዎች የጋራ ጉባኤ፣ የተጠቃለለ አገራዊ የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም፣ በሶስት ክልልሎች የተደረገ የመዝገብ ኦዲት ሪፖርት ፣ የተጠቃለለ የ2017 በጀት ዓመት የፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት እና የፍትሕ ሚኒስቴር የ5ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ቀርቦ ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጓል፡፡
በጉባኤው መሰረተ ማህበረሰብ ፍትሕ አገልግሎትን ከማጠናከር አንፃር፤ የወንጀል ፣ የአስተዳደር እና የፍትሐብሔር ፍትሕ ሥርዓትን በአዲስ አስተሳሰብ ከመምራት፤ ያደገ እና ውጤታማ የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ከማሳደግ፤ የተጠናከረ ንቃተ-ህግ ትምህርትና የሕግ ድጋፍ ማድረግን በተመለከተ፤ ዘመናዊ አማራጭ የሙግት መፍቻ ሥርዓቶችን ከማስፋት፤ የክልል ፍትሕ አካላት ተቋማትን በዞኖችና በወረዳዎች ያላቸውን ተደራሽነት ማስፋፋትን በተመለከተና ሌሎች የፍትሕ ዘርፍ የትራንስፎርሜሽን አምድ የሆኑ እና ሲከናወኑ የነበሩ ሥራዎች አፈፃፀም በሰፊው ተዳሰዋል፡፡
በማጠቃለያም በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ቅንጅታዊ አሰራሮችን መዘርጋትና ማጠናከር፤ የአማራጭ ቅጣትና መልሶ መቀላቀል፤ ከህግ ማርቀቅ ሂደት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራ፤ ተገልጋይ ተኮር የሆነ የአገልግሎት አሰጣጥ መዘርጋት፤ ተቋማዊ አደረጃጀትና የሰው ሃይሉን የማሻሻል ስራዎችን አስመልክቶ በትኩረት ሊተገበሩ የሚገቡ ጉዳዮች ላይ በበላይ አመራሩ አቅጣጫ ተስጥቷል፡፡
በመጨረሻም የጉባኤው ተሳታፊዎች በድሬዳዋ ከተማ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶችን እና ታሪካዊ ስፍራዎችን በመጎብኘት ጉባኤው ተጠናቋል፡፡