ሶስተኛው አገር አቀፍ የፍልሰት ምርምር ጉባዔ በመቀሌ ከተማ ተካሄደ

Third National Migration Research Conference Held in Mekelle City

በብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ማዕቀፍ በየዓመቱ የሚካሄደው አገር አቀፍ የፍልሰት ምርምር ጉባዔ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በመቀሌ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ ትብብር ጥምረት ጽ/ቤትና በትምህርት ሚኒስቴር አስተባባሪነት ከዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት እና ከጀርመን ተራድዖ ድርጅት በተገኘ ድጋፍ የተካሄደውን በዚህ የፍልሰት ምርምር ጉባዔ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ጉባዔውን በንግግር የከፈቱት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት ክቡር አቶ አማኑኤል አሰፋ እንደተናገሩት፤ የፍልሰት ጉዳይ በተለይም መደበኛ ያልሆነው የሰዎች ዝውውር የክልሉ፣ የአገሪቱ እና የመላው ዓለም አሳሳቢና ወቅታዊ ችግር ሆኗል፡፡

እንደ ክቡር ምክትል ፕሬዝደንቱ ገለጻ የትግራይ ክልል በተለይም በምስራቁ የፍልሰት መንገድ በሕገ-ወጥ መንገድ ለሚጓዙ ፍልሰተኞች መነሻ እንደመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ የሚመለከታቸውን አካላት ያሳተፈ ጠንካራ ስራ ማከናወን ያስፈልጋል፡፡

በትግራይ ክልል በጦርነቱ ማግስት የበርካታ ወጣቶች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሕይወት አደጋ ላይ በመውደቁ ምክንያት መደበኛ ላልሆነ የፍልሰት ጉዞ በመዳረግ ላይ መሆናቸውን የጠቀሱት ምክትል ፕሬዝደንቱ፤ የፍልሰት ምርምር ጉባዔው በክልሉ መዲና መቀሌ መካሄዱ ችግሮቹና የምላሽ አሰጣጦቹ የተመራማሪዎችንና የፖሊሲ አውጪዎችን ትኩረት እንዲያገኙ እንደሚያግዝ ገልጸዋል፡፡

የኢፌዴሪ የፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋን መልዕክት ያስተላለፉት የብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም አያሌው በበኩላቸው በፍልሰት ዙሪያ የሚከናወኑ ጥናትና ምርምሮች መደበኛ ፍልሰትን ለማበረታታትና ኢ-መደበኛ የሆነውን ፍልሰት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የሕግና የፖሊሲ እንዲሁም የአደረጃጀት ማዕቀፎችን ለመዘርጋት ጠቀሜታቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ አብርሃም ገለጻ በአገራችን በፍልሰት ዙሪያ በርካታ ጥናቶችና ምርምሮች ቢደረጉም፣ ጥናት እና ምርምሮችን ለማሰባሰብ እንዲሁም ምርምሮች የሚደገፉበትና ለፖሊሲና ለሕግ መነሻ እንዲሆኑ የሚያስችል ሥርዓት አልተዘረጋም። በመሆኑም ምርምሮች በግለሰቦች፣ በጥናትና ምርምር እና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ተበታትነው ይገኛሉ፡፡

በዚህ መነሻ ጥናትና ምርምሮቹ በፍልሰት አስተዳደር ሥርዓቱ ውስጥ ሊያበረክቱ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ባለመቻላቸው ብሔራዊ የትብብር ጥምረቱ ከፍልሰት ምርምር የስራ ቡድን ሰብሳቢ የትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡

ከእነዚህም ውስጥ አንዱ በየዓመቱ አገር አቀፍ የፍልሰት ምርምር ጉባዔ እንዲዘጋጅ ማድረግ ሲሆን፤ የመጀመሪያው ጉባዔ በ2015 ዓ.ም. በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ አስተናጋጅነት፣ ሁለተኛው በአዲስ አበባ መካሄዳቸውን አስታውሰዋል፡፡

የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ዶክተር ሃና ሃጎስ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲያቸው ለፍልሰት ምርምርና ትምህርት ልዩ ትኩረት በመስጠት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸው፣ ይህንን አገራዊ መድረክ ማዘጋጀታቸውም ለጥረቶቹ ዕውቅና የሚሰጥ መሆኑን አውስተዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴዔታ ክቡር አቶ ኮራ ጡሹኔ በተወካያቸው አማካኝነት መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፤ ዓለም አቀፉን የፍልሰት ድርጅት በመወከል ደግሞ የድርጅቱ የትግራይ ኃላፊ ሚስተር አቡበክር ኢብራሂም የአጋርነት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ሰኔ 11 እና 12 /2017 ዓ.ም. የተካሄደው ይህ መድረክ የፌደራልና የክልል የፖሊሲ አውጭዎችን፣ በፍልሰት ዙሪያ ምርምር የሚያካሂዱ እና የፍልሰት ትምህርትን የሚሰጡ የአገራችን ዩኒቨርሲቲዎችን፣ የጥናትና ምርምር ተቋማትን እንዲሁም አጋሮችን ያሰባሰበ የምርምር ጉባዔ ሲሆን፤ በመድረኩም በተለያዩ የፍልሰት ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በቀረቡ የምርምር ፅሁፎች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡

Tagged Under: academic research Addis Ababa University agency conference development german human Human Trafficking international international organization for migration irregular Irregular migration legal framework mekelle mekelle university Migration ministry of education national policy organization policy makers region Research Research Conference researchers Tigray tigray region trafficking
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች