የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. በፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ኤርምያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) ስዊድን የፍልሰት ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ጆሀን ፎርሴል እና በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደርን ክቡር ማግነስ ሌናርትሰንና የልዑክ ቡድናቸው ጋር በፍልሰት የሁለትዮሽ ትብብር ጉዳዮች ዙሪያ ሚያዝያ 14/2018 ዓ.ም ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት የስዊድን የፍልሰት ሚኒስቴር ሚንስትር ክቡር ጆሀን ፎርሴል ከልዑክ ቡድናቸው ጋር በኢትዮጵያ ውስጥ በጣም ጥሩ የሚባል የልማት ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን እና አገሪቱ በኢኮኖሚ እያደገች መምጣቷን መታዘብ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
በሁለቱ አገራት መካከል ዘመናት የተሻገረውን የጋራ ትብብር አጠናክረው መቀጠል እንደሚፈልጉና በኢትዮጵያ ባለው የፍልሰት ስርዓት ውስጥ ተሳትፎ በማድረግ በሕብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው የፍልሰት ሥርዓት እንዲገነባ ለማድረግ በጥምረት የመስራት ፍላጎት እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡ ከዚሁ በተጨማሪም አገራቸው ከፍልሰት ጋር የተያያዙ የአቅም ግንባታ፣ የንግድ፣ የስራ ፈጠራ፣ የኢንቨስትመንት እና ሌሎች መስኮች ላይ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላት ጠቁመዋል፡፡
ክቡር ኤርምያስ የማነብርሃን(ዶ/ር) በበኩላቸው በፍልስት በኩል ህጋዊ ያልሆነ ፍልሰትን ለመከላከል በአገራችን በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰው። በተለይም ህጋዊ ባልሆነ መንገድ ከአገር የሚወጡ ዜጎች በማስመልከት ወደ ተነሱበት አካባቢ ተመልሰው ከማሕበረሰቡ ጋር እንዲቀላቀሉ ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ የፌዴራልና የክልል አስፈጻሚ አካላት በተሳተፉበት ብሔራዊ የትብብር ጥምረት ተቋቁሞ ፍልሰት ደህንነቱ የተጠበቀ፣ የተደራጀ እና ህጋዊ እንዲሆን ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን አስታውሰዋል፡፡
አክለውም ከስዊድን መንግስት ጋር በሁሉም የፍልሰት ጉዳዮች ላይ ስትራቴጂያዊ ውይይት ለመድረግ በፍትሕ ሚኒስቴር በኩል ፍላጎት መኖሩን በመግለፅ፣ ህገወጥ ፍልሰትን ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የአቅም ግንባታ ስራዎችን፣ ለኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መጠለያ እና ሁለንተናዊ እርዳታ በመስጠት፣ ከአውሮፓ የሚመለሱ ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እና እንዲቋቋሙ በማድረግ ረገድ፣በፍልሰት ፖሊሲ ዝግጅት እና ተያያዥነት ያላቸው ተግባራት ላይ የሁለትዮሽ ትብብር ግንኘነቱን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡