በሰው የመነገድ ወንጀልን በመከላከልና ሕግ ማስከበር ዙሪያ በአውሮፓ ሕብረት የፍትሕና የፖሊስ ተቋማት የልምድ ልውውጥ መድረክ ተካሄደ

Exposure Visit on Combating Trafficking in Persons and Smuggling of Migrants and Strengthening Law Enforcement Held with European Union Institutions

በፍትሕ ሚኒስቴር አስተባባሪነት በሰው የመነገድና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን ላይ በሚካሄዱ የምርመራና ክርክር ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረቱን ያደረገ የሕግ አስከባሪ አካላት የልምድ ልውውጥ መድረክ ተካሂዷል፡፡

የልምድ ልውውጥ መድረኩ እኤአ ማርች 16-18/2026 ዓ.ም. በኔዘርላንድስ ዘ ሔግ ከተማ በሚገኙት የአውሮፓ ሕብረት የፖሊስ ተቋም (Europol) እና በሕብረቱ የወንጀል ፍትህ ትብብር መስሪያ ቤት (Eurojust) እንዲሁም በኔዘርላንድስ የፍትሕ ሚኒስቴር የዓቃቤ ሕግ ተቋም ዋና መስሪያ ቤቶች የተካሄደ ሲሆን፤ የፍትሕ ሚኒስቴር የሚመከለከታቸው የሥራ ክፍል ኃላፊዎች እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ከዩሮፖል ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ Mr. Gurgen Ebner እና ከዩሮጀስት ዋና ዳይሬክተር Mr. Michael Schmid እና ምክትላቸው Margarita Sniytyte-Daugeliene እንዲሁም ከኔዘርላንድስ የአቃቤ ሕግ መስሪያ ቤት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

በተመድ የአደገኛ ዕፆችና ወንጀሎች መቆጣጠሪያ ቢሮ (UNODC) ድጋፍ በተካሄደው በዚህ መድረክ በአውሮፓ ሕብረት እንዲሁም በኔዘርላንድስ መንግስት አማካኝነት እየተከናወኑ ያሉ የሕግ ማስከበር ስራዎች በተለይም በዋና ዋና የፍለሰተኞች መተላለፊያ መስመሮች በወንጀል መረብ እና በቀንደኛ ተጠርጣሪዎች ላይ የሚያተኩር እንዲሁም በመረጃ (ኢንተለጀንስ) ላይ የሚመሰረት ወንጀል ምርመራ እንዲሁም በሕግ አስከባሪ አካላትና በአገራት መካከል ስለሚኖር ትብብር ሰፊ ልምድ ለመቅሰም ተችሏል፡፡

ኢትዮጵያ በተለይም በሰሜኑ የፍልሰት መስመር መዳረሻቸውን አውሮፓ ለሚያደርጉ መደበኛ ያልሆኑ ፍለሰተኞች መነሻና መተላለፊያ አገር በመሆኗ ከአውሮፓ ሕብረትና ከአባል አገራቱ ጋር ሁሉን አቀፍ የሆነና ጠንካራ ትብብር እንደሚያስፈልግ ከኢትዮጵያ ልዑካን በኩል ገለጻ ተደርጓል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ በሕግ ማስከበር ረገድ በተቋማት መካከል ቅንጅትን ለማጠናከር፣ ተጠርጣሪዎችን ለሕግ ለማቅረብና ከመተላለፊያና መዳረሻ አገራት ጋር በሕግ ጉዳዮች ጠንካራ ትብብር ለመፍጠር በርካታ ጅምር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በሕግ ማስከበር ረገድ ያሉ ተግዳሮቶችም ዙሪያ ማብራሪያ ቀርቧል፡፡

ከዚህ ቀደም ከሁለቱም የአውሮፓ ሕብረት የሕግ አስከባሪ ተቋማት ጋር ምንም ዓይነት የቅንጅትና የትብብር ሥራዎች እንዳልነበሩ በመደረኩ የተገለጸ ሲሆን፤ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው ይህ የልምድ ልውውጥ መድረክም በቀጣይ ጠንካራ የትብብር ማዕቀፎችን ለመዘርጋት ፈር ቀዳጅ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡ ዋና ዋና የጋራ የትብብር መስኮችም በውይይቶቹ ተለይተዋል፡፡ ዩሮፖልና ዩሮጀስትም ወደ አውሮፓ ለሚገቡ ፍልሰተኞች መተላለፊያና መነሻ አገር ከሆነችው ከኢትዮጵያ ጋር በሕግ ማስከበር ረገድ በተለይም በቴክኒክ ድጋፍ እንዲሁም በመረጃ (ኢንተለጀንስ) ልውውጥ ዙሪያ በትብብር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

በተያያዘ የልዑካን ቡድኑ በኔዘርላንድስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፍልሰት ጉዳዮች ቢሮ በመገኘት አገራችን እያከናወነች ያለውን ስራ እና የኔዘርላንድስ መንግስት በተለይም በCOMPASS ፕሮግራም አማካኝነት እየደረገ ያለውን ድጋፍ በተመለከተ ገለጻ ያደረገ ሲሆን፤ በቀጣይ በጋራ በሚከናወኑ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

ተቋማችን በአዋጅ ቁጥር 1178/12 መሰረት በሰው የመነገድና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተለይም በሕግ አስከባሪ አካላት መካከል ጠንካራ ቅንጅታዊ አሰራር እንዲኖር እንዲሁም በዋና ዋና የወንጀል ፈጻሚዎች ላይ የሚካሄደው የሕግ ማስከበር ርምጃ እንዲጠናከር ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ እየሰራ ይገኛል፡፡

ይህንኑ የአስተባባሪነት ሚናውን እንዲወጣ ለማድረግና በተያዘው በጀት ዓመት የተጀመረውን ጠንካራ የሕግ ማስከበር ርምጃ ለማገዝ በዕቅድ እያከናወናቸው ከሚገኙት ተግባራት አንዱ የሆነው ይህ የሌሎች አገራትን ልምድ የመቅሰም ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን፤ በቀጣይም የባለሙያዎች ቡድን ወደ ሌሎች አገሮች በመሄድ ልምድ እንዲቀስሙ የሚደረግ ይሆናል፡፡

Tagged Under: act cement combating decree enforcement eu euro european European Union exposure force grant institution institutions itu law Law Enforcement legislation migrant migrants mr. pea per person persons proclamation smuggling of migrants statute trafficking in persons un
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች