በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ብሔራዊ የትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ከዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት (IOM) ጋር በመተባበር በሠራተኛ ፍልሰት እና የውጪ አገር ስራ ስምሪት አስተዳደር ዙሪያ ከብሔራዊ ጥምረት አባል ተቋማት ተወካዮች ጋር የምክክር መድረክ አካሄደ።
በዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት (IOM) የJoint Labour Migration Program (JLMP) አስተባባሪ የሆኑት ሚስተር ኤድዊን ሪጋ ባስተላለፉት መልዕክት ከምስራቅ አፍሪካ በፖለቲካ አለመረጋጋት እና ተያያዥ ምክንያቶች በርካታ ዜጎች የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ ሌሎች ሀገራት የሚሄዱ ቢሆንም በአብዛኛው በሥራ ፈልሰው በሚሄዱበት አገር መብታቸው እና ክብራቸው አይጠቅላቸውም ብለዋል፡፡ አያይዘውም እነዚህ ዜጎች መብታቸው ተረግጦም ቢሆን ገንዘብ በመላክ የሃገራቸውን ኢኮኖሚ የሚደግፉ በመሆኑ ሀገራት የዜጎቻቸውን መብት ለማስጠበቅ የስራ ፍልሰት አስተዳደር ሊኖራቸው ይገባል፤ ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶችን መፈረም እና ህጎችን ማውጣት እንዲሁም ዜጎቻቸው ከሚኖሩባቸው ሃገራት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት ማድረግ እንደሚገባቸው አውስተዋል፡፡ Joint Labour Migration Program (JLMP) ሃገራት የተሻለ የፍልሰት አስተዳደር እንዲኖራቸው በማገዝ ላይ እንዳለ ባደረጉት በመልዕክታቸው ገልፀዋል፡፡
ፍልሰት የሀገራትን ግንኙነት የሚያጠናክር በመሆኑ የሥራ ፍልሰትን ለመምራት ትብብር ሊኖር እንደሚገባ በመጠቆም የትብብር ጥምረቱን ማበረታታትና ማጠናከር እንደሚገባ እና የአፍሪካ ህብረትም ይህንን እንደሚደግፍ የገለፁት ደግሞ በአፍሪካ ህብረት የJLMP አስተባባሪ የሆኑት ሚስስ ኦደቴ ቦሊ ናቸው፡፡
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ብሔራዊ የትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አብርሃም አያሌው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ኢትዮጵያ የስራ ፍልሰት አስተዳደርን ለማሻሻል የሚያግዙ ዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ስምምነቶችን ከመፈረሟም በላይ ብሔራዊ ም/ቤት እና ብሔራዊ የትብብር ጥምረትን በአዋጅ በማቋቋም ስራዎችን በመከናወን ላይ እንዳለች ገልፀዋል፡፡ አቶ አብርሃም አክለዉም በተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች አማካኝነት ህጋዊ የስራ ፍልሰትን ለማበረታታት እና የውጪ አገር የስራ ስምሪትን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን እና ከኢትዮጵያ ለሥራ ወደ ሌላ አገር የሚሄዱ ፍልሰተኞች በሚሰሩባቸው ሀገራት መብታቸው እንዲጠበቅ የሚያስችሉ የሁለትዮሽ ስምምነትን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነና ኢትዮጵያ በሥራ ፍልሰት አስተዳደር ውስጥ የሚሰሩ የመንግሥት ተቋማትና ባለድርሻ አካላት በጋራ የሚሰሩበትን ሁኔታ በመፍጠር እየሰራች እንደምትገኝ ገልፀዋል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር ዐቃቤ ሕግ የሆኑት አቶ ዮሃንስ ሲሳይ በኢትዮጵያ የሥራ ፍልሰት አስተዳደር የአሠራር እና የአደረጃጀት ማዕቀፎችን ያቀረቡ ሲሆን የሕግ ማዕቀፎችን በተመለከተ ደግሞ በዐቃቤ ሕግ እያሱ ቀለሜ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በምክክር መድረኩ የጥምረቱ አባል ተቋማትን ጨምሮ የመንግሥት መ/ቤቶች እና ማህበራት ሲሳተፉ የኢጋድ፣ የኬንያ እና የኡጋንዳ ተወካዮችም ተሞክሮዎቻቸውን አጋርተዋል፡፡