በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ከዓለም ዓቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት(IOM) በጋራ ያዘጋጁትና በዓለም ዓቀፉ የፍልሰት ስምምነት ( Global Compact on Migration) አገራዊ የትግበራ ዕቅድ ዝግጅት ላይ ያተኮረ የከፍተኛ ኃላፊዎች የምክክር መድረክ ጥር 16/2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን በመከላከልና መደበኛ ፍልሰትን በማበረታታት እንዲሁም የዜጎችን ደህንነትና ሰብዓዊ መብት ለማክበርና ለማስከበር ዓለም አቀፉን የፍልሰት ስምምነት (Global Compact on Migration-GCM) በመፈረምና በተለያዩ ሀገራዊ የህግ ማዕቀፎች፣ ፖሊሲዎች፤ ስተራቴጂዎችና ፕሮግራሞች በማካተት ተግባራዊ ስታደርግ መቆየቷ ተገልጿል፡፡
ይሁንና በጉዳዩ ላይ የተደረጉ የዳሰሳ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የክትትልና ግምገማ ስርዓት ያካተተ ማዕቀፍ ያልተበጀ በመሆኑ ስምምነቱን በተፈለገው ደረጃ ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር ክፍተቶች እንዳሉ ተወስቷል፡፡
ይህ የምክክር መድረክም የስምምነቱ የትግበራ ዕቅድ ዝግጅት ከመጀመሩ አስቀድሞ እስካሁን በተሠሩ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እና በትግበራ ዕቅዱ አስፈላጊነት ላይ በመምከር ግብዓት ለማሰባሰብ እና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጠ ያለመ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
በዓለም ዓቀፍ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ የተስተካከለ እና መደበኛ ፍልሰት ስምምነት” (Global Compact for Safe, Orderly and Regular Migration – GCM) አጠቃላይ ገጽታ፤ በኢትዮጵያ የስምምነቱ የትግበራ ዕቅድ ዝግጅቱ ያለበትን ደረጃ፤ የስምምነቱን አገራዊ የትግበራ እቅድ አስፈላጊነት እና ጠቀሜታ፤ እስካሁን የነበረዉን የዝግጅት ሂደት እና የተሠሩ ስራዎችንና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን አስመልክቶ ለተሳታፊዎች ሪፖርት የቀረበ ሲሆን፤ አስፈላጊ ናቸዉ የተባሉ ምክረ ሀሳቦችም በዉይይት መድረኩ ላይ ተንጸባርቀዋል፡፡
በመጨረሻም ከመድረኩ ከተሳታፊዎች በርካታ ጥያቄዎች ቀርበዉ ምላሽ የተሰጠ ሲሆን፤ ምክክሩ ዉጤታማ እንደነበረና ለቀጣይ ሥራዎች አጋዥ የሆኑ ግብዓቶች የተገኙበት እንደነበረም ተገልጿል፡፡ በምክክሩ የተገኙትን ግብዓቶች ጨምሮ በቀጣይ በሚሰሩ ሥራዎች ላይ ወሳኝ ናቸዉ የተባሉ አቅጣጫዎችም ተመላክተዋል፡፡