ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሕገ መንግስቱንና ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን ከማክበርና ማስከበር፣ የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ እንዲሁም የፌዴራል መንግስቱንና የሕዝብን የፍትሐ-ብሔር ጥቅም ከማስከበር አንፃር ባለፉት 9ወራት ውስጥ በርካታ ተግባራትን ስለማከናወኑ ሚየዝያ 11 ቀን 2ዐ15 ዓ.ም በተካሄደው የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ላይ ተገልጿል፡፡
በመድረኩ የተቋሙ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች እንዲሁም ቡድን መሪዎችና አስተባሪዎች የተገኙ ሲሆን የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ፣ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ እና የሃብት አስተዳደር የ9 ወር የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት እና የቀጣይ የ3 ወራት የትኩረት አቅጣጫ በዝርዝር ቀርቧል፡፡
የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የ9 ወራት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት በዘርፉ ጽ/ቤት ኃላፊ በአቶ በረከት ማሞ የቀረበ ሲሆን የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ ወንጀል የፈጸሙ ግለሰቦችን ለሕግ ከማቅረብና ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ከማድረግ፣ በሙስና ወንጀል የተመዘበሩ የሕዝብና የመንግሥት ሐብት ከማስመለስ እንዲሁም የተለያዩ የፍትሕ አገልግሎትን ከመስጠት አንፃር ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸው ተገልጿል፡፡
የወንጀል ምርመራ መዝገቦች አፈጻፀም በተመለከተም በ24,528 መዝገቦች ላይ ዐቃቤ ሕግ የተለያዩ ውሳኔዎችን የሰጠ በመሆኑ የምርመራ መዝገቦችን የማጥራት ምጣኔ አፈጻፀም በአማካይ 89% ማድረስ መቻሉ፣ በሁሉም ወንጀል ጉዳዮች በመዝገብ የማስቀጣት ምጣኔ ደግሞ 96.96% በመቶ አፈፃፀም የተገኘ መሆኑ እንዲሁም በሴቶችና ሕፃናት በሚፈፀሙ የልዩ ልዩ ወንጀሎች ዙሪያ ምርመራቸው ተጠናቀው በቀረቡ 529 መዛግብት በሁሉም ላይ ዐቃቤ ሕግ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው የተደረገ መሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡ በሙስና ወንጀሎች ምክንያት የተመዘበሩ የሕዝብና የመንግሥት ሐብት ከማስመለስ አኳያ በተለያዩ ወንጀሎች የተሳተፉ ወንጀለኞች ንብረትን ለይቶ እንዲታገዱ እና በሕጋዊ መንገድ እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉም ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም በልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች፣ በሴቶችና ሕፃናት በሚፈፀሙ ወንጀሎች፣ በምስክሮችና ተከሳሾች አለመቅረብ የሚቋረጡ መዛግብት መቀነስ፣ ከሙስና፣ ከኢኮኖሚ እንዲሁም ከተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች አኳያ የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገብ የተቻለ ስለመሆኑ፣ በተጨማሪም የሕግ ኦዲትና ኢንስፔክሽን ሥራን ማጠናከር፣ በወንጀል የተገኘ ሃብትን ማስመለስ፣ የወንጀል ምስክሮች፣ ጠቋሚዎች እና ተጎጂዎች አገልግሎት አሰጣጥን ማሳደግ ስለመቻሉ በሪፖርቱ ተዘርዝሯል፡፡
የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ የ9 ወራት አፈፃፀም ሪፖርት በመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ አማካሪ የሆኑ ወ/ሪት ሀወኒ ታደሰ ያቀረቡ ሲሆን የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎችንና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በሕግ ጥናት፣ በፍትሐ ብሔር ጉዳዮች፣ በንቃተ ሕግና ሥልጠና፣ በሴቶች፣ ህጻናትና ባለብዙ ዘርፍ ተግባራት፣ በትብብር ጥምረት፣ በሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሀ ግብርና ሌሎች በርካታ ስራዎች ዙሪያ የተጠናከረ ተሳትፎ እንዲያደርጉ እድል የተፈጠረ መሆኑን ገልጸው የወንጀልና ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መከላከል፣ ይቅርታና አመክሮ አፈጻጸም ክትትልና ውጤታማነት፣ የመንግሥትና የሕዝብን ፍትሐ-ብሔራዊ ጥቅም ማስከበር፣ በሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ዓለም ዓቀፍ ትብብር ማጠናከር፣ የፌዴራል ሕጎች ተፈጻሚነትን ማጎልበት፣ የሕግ ጥናት፣ ማርቀቅና ምክር አፈጻጸም ማጠናከር ላይ ልዩ ልዩ ተግባራት እንደተከናወኑ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም የነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት አሰጣጥ ተደራሽነትን ማሻሻል፣ የጥብቅና አስተዳደርና ክትትልን ማጠናከር፣ ለንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ የሚቀርቡ የይግባኝ ቅሬታዎች ውሳኔ አሰጣጥን ማሻሻል፣ በንግድ ውድድር፣ ሸማቾች መብትና በምርት ገበያ ዙሪያ ለዳኝነት ችሎቱ የሚቀርቡ ክሶች የውሳኔ አሰጣጥን ቀልጣፋ ማድረግ እንዲሁም ዘመናዊ አሠራርንና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራትም በተሻለ ደረጃ ስለመከናወናቸው በዘርፉ ሪፖርት ተጠቅሷል፡፡
የተቋሙን የሀብት አስተዳደር አፈጻጸም በተመለከተ የሀብት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ የኋላሸት አግዝ ያቀረቡ ሲሆን በተለይም አገልግሎትን ለማዘመን የኢ-ፔይመንት፣ የሲቪል ሰርቪስ የተቀናጀ የመረጃ ስርዓት አጠቃቀም፣ የኢ- ጂፕ፣ የውስጥ ትራንስፖርት ስምሪት ሲስተም የመዘርጋት፣ የንብረት ማስወገድ እንዲሁም የተለያዩ የውስጥ አሠራር ጥናት ማድረግና የአሠራር ስርዓት የመቅረጽ ከተከናወኑት ተግባራት መካከል ዋነኛዎቹ መሆናቸው በቀረበው ሪፖርት ተመላክቷል፡፡
የሪፖርቶቹን መቅረብ ተከትሎ ተሳታፊዎች ውይይት ያደረጉ ሲሆን የቀጣይ የ3 ወራት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ጠንክሮ መሥራት እንደሚያስፈልግ በአፅንዖት ተገልጿል፡፡