በሀገራችን ኢንቨስትመንትን መነሻ አድርገው በሚቀርቡ ቅሬታዎች፣ አለመግባባቶች እና አለም አቀፍ ክርክሮች አያያዝ እና አመራር ዙሪያ ውይይት ተካሄደ

Discussion Held on the Handling and Management of Investment-Related Grievances, Disputes, and International Arbitrations in Our Country

የውይይት መድረኩን በመልዕክታቸው ያስጀመሩት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ መድረኩ የተዘጋጀበትን ዓላማ ሲገልጹ ፍትሕ ሚኒስቴር በሕግ ከተሰጡት ዘርፈ ብዙ ሥልጣን እና ኃላፊነቶች መካከል የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. መንግሥት በዓለም ዓቀፍ የዳኝነት ሰጪ አካላት ዘንድ በሚከስባቸው ወይም በሚከሰስባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መንግሥትን በመወከል ክስ/መልስ የማቅረብ፣ ክርክር የማድረግ፣ ድርድር የማከናወን እና ውሳኔዎችን ማስፈጸም አንዱ መሆኑን ጠቅሰው ኢንቨስትመንትን መነሻ አድርገው በሀገራችን ላይ የሚቀርቡ ዓለም ዓቀፍ ክርክሮች በሚመሩበት እንዲሁም አማራጭ በሆኑ መንገዶች ክርክሮቹ በሚፈቱበት ሂደት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅት ያስፈልጋል ብለዋል።

በተለያዩ ጊዜያት ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ የኢንቨስትመንት ክሶች በሀገራችን ላይ እየቀረቡ ይገኛሉ ያሉት ሚኒስትሩ እስካሁን ለቀረቡት ክሶች ፍትሕ ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው ጋር በመቀናጀት ምላሽ በመስጠት እና በመከራከር እንዲሁም በመደራደር ሂደት ሰፊ ተሳትፎ ማድረጉን ገልጸዋል። ኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻ በማድረግ ረገድ ሰፊ ጥረቶች በሚደረጉበት በዚህ ወቅት የኢንቨስትመንት ክሶች መበራከት አሉታዊ ጎኑ ያመዝናል ብለዋል።

ዶ/ር ጌዲዮን አክለውም ክርክሮቹ እንደሀገር ሊፈጥሩ ከሚችሉት የተዛባ ምስል በተጨማሪ ከፍተኛ ውጪ ሊያስወጡ የሚችሉ እንደመሆናቸው እንደሀገር ያለንን የኢንቨስተሮች ቅሬታ እና አቤቱታ አፈታት ስርዓት በማሻሻልና በማጎልበት እንዲሁም አለመግባባቶችን በአማራጭ መንገድ በመፍታት ክርክሮችን ከምንጫቸው ማድረቅ ይገባናል። ከዚህ አልፈው ወደክርክር የሚያመሩ ጉዳዮችንም የሀገራችንን መብት እና ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ በቅንጅት የመያዝ እና የመምራት የተናበበ አሠራርን መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ተሳትፎ የሚያደርጉ የፌዴራል፣ የክልል እና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች እና ከፍተኛ ባለሞያዎች እንዲሁም በዘርፉ ልምድ ያላቸው ግለሰቦች ተሳትፈዋል። ለውይይቱ መነሻ የሚሆኑ ሀገራችን በተፈራረመቻቸው የሁለትዮሽ ስምምነቶች፣ በኢንቨስትመንት ቅሬታ አያያዝ ስርዓት፣ በአማራጭ የአለመግባባት አፈታት እና በክርክሮች አያያዝና አመራር ዙሪያ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በዘርፉ ላይ ሰፊ የግንዛቤ ክፍተት መኖሩን፣ ተቋማት በውሳኔ አሰጣጥ ሂደት የማይናበቡ መሆኑን፣ የሕግ አተገባበር መላላት፣ የኢንቨስተሮች ልየታ ክፍተት እና የመሳሰሉ ችግሮች መኖራቸውን አንስተዋል።

የውይይት መድርኩን በማጠቃለል መልዕክት ያስተላለፉት የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ አለምአንተ አግደው ሀገራችን ለኢንቨስትመንት ምቹ የሚያደርጓት እምቅ ኃብቶች ያሏት፣ ሰፊ ህዝቧ ጥሩ የገበያ አማራጭን የሚፈጥር፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው አምራች ኃይል ያለባት፣ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መሆኗ፣ በአለም ላይ ተወዳዳሪ የሆነ አየር መንገድ፣ የመሳሰሉት መኖራቸው ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ ከፍተኝ አስተዋጾ ያበረክታሉ ብለዋል።

አክለውም እንደሀገር በዘርፉ በሚሰማሩ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮች መካከል ያለውን መብትና ጥበቃ ሚዛናዊ እንዲሆን የማድረግ፣ የኢንቨስተሮች ልየታ ስራን በቁ በሆነ ምርመራ የመምራት፣ ኢንቨስተሮች የሀገራችንን ህጎች እንዲያከብሩ የመከታተል፣ ቅሬታ እና አለመግባባቶችን በአፋጣኝ የመፍታት፣ በዘርፉ ሰፊ ግንዛቤን የመፍጠር ስራን የመሥራት እና በተቋማት መካከል ተገቢውን ቅንጅታዊ አሠራር የማዳበር ስራዎች በስፋት ሊተኮርባቸው እና ሊሰራባቸው የሚገባ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይ በሁሉም ባለድርሻ ተቋማት መከናወን አለባቸው ያሏቸውን ጉዳዮች አቶ አለምአንተ በዝርዝር ሲያስቀምጡ ሁሉም ተቋም ለዘርፉ ያላበትን ኃላፊነት በአግባቡ በመለየት ለኢንቨስትመንት ማነቆ ሊሆኑ የሚችሉ አሰራሮችን እንዲያሻሽል፣ ቅሬታዎችን በአግባቡ እና በአፋጣኝ እንዲያስተናግድ፣ በኃላፊነቱ ዙሪያ ግንዛቤ የመፍጠር ስራን እንዲሰራ፣ ቅሬታዎች እና አለመግባባቶችን በመፍታት ረገድ እንዲሁም ለሚቀርቡ ክሶች ተገቢውን መልስ በማዘጋጀት ሂደት የሚፈለጉ መረጃ እና ማስረጃዎችን በፍጥነት በማቅረብ እና ለሚጠየቁ የትብብር ጥያቄዎች ሁሉ አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጡ አሳስበው ብርቱ የሆነ የእርስ በርስ ሚናን የለየ ቅንጅት እንዲፈጥርም አክለው ገልጸዋል።

ፍትሕ ሚኒስቴርም በሁለትዮሽ ስምምነቶቹ ዙሪያ እየተደረገ በሚገኘው ጥናት ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንደሚቀጥል፣ በቅሬታ እና አለመግባባት አፈታት ዙሪያ ብርቱ ቅንጅታዊ ተሳትፎ እንደሚያደርግ፣ በህጎቻችን ዙሪያ አዳዲስ ለሚመጡ ኢንቨስተሮች በሚመች መልኩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እንደሚያመቻች፣ የሚመለከታቸው ተቋማት የሕግ ክፍሎች ለዘርፉ ጉልህ ሚና እንዲጫወቱ አቅማቸውን የማጎልበት ስራ እንደሚሰራ፣ ሌሎች ተመሳሳይ የውይይት መድረኮችንም እንደሚያመቻች ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።

የተቋማት ቅንጅትንም በተመለከተ የክልል እና የፌዴራል የሚመለከታቸው ተቋማት በጉዳዩ ዙሪያ ለመምከር እንዲችሉ ቋሚ የሆነ የመገናኛ መድረክ እንዲኖራቸው እንዲሁም ስራቸውን በቅንጅት መሥራት የሚያስችላቸው የአሠራር ስርዓት/ማኑዋል በጥናት ላይ ተመስርቶ መነሻ እንደሚያዘጋጅ እና ከሁሉም ባለድርሻ ጋር በአጭር ጊዜ ተገናኝቶ በመምከር አሰራሩ ተግባራዊ እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ገልጸዋል።

በመጨረሻም በመድረኩ ላይ የተሳተፉትን አመራሮችና ባለሞያዎች፣ የመወያያ ጽሁፍ አቅራቢዎች፣ አወያዮች እና የመድረክ አዘጋጆች እንዲሁም ለመድረኩ መሳካት የፋይናንስ ድጋፍ ያደረጉ ተቋማት እና ድርጅቶችን በማመስገን የውይይት መድረኩ ተጠናቅቋል።

Tagged Under: adr agreements alternative alternative dispute resolution (adr) Arbitration bilateral contract enforcement dispute Dispute Resolution disputes foreign Foreign Investment framework government regulation international International Arbitration Investment investment agreements investment disputes Investment Promotion investor protection legal legal framework Legal Reforms resolution stakeholder coordination treaties
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች