የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር ብሔራዊ የትብብር ጥምረት ጽ/ቤት እና የዓለም የፍልሰት ድርጅት (IOM) በመተባበር የተዘጋጀ ብሔራዊ የፍልሰት ምክር ቤት ዓመታዊ ስብሰባ ተካሂዷል፡፡
የተለያዩ የፌደራል ተቋማትና የክልል አስተዳደር ተወካዮች በተገኙበት በተካሄደው በዚህ ሰብሰባ ላይ ተገኝተው የእንኳን ደህ መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር ሚንስትር ክብርት ወ/ሮ ሀና አርአያስላሴ የፍልሰት አስተዳደር ጉዳዮች አካል የሆነው ብሔራዊ ምክር ቤት በሰው የመነገድና ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን በመከላል፣ ሕግ በማስከበር፣ በተጎጂዎች ድጋፍና መልሶ ማቋቋም፣ ሕጋዊ የውጪ አገር የሥራ ስምሪት እንዲሁም የፍልሰትና ልማት ጉዳዮች በሚመከሩበት መድረክ ላይ የተገኙ እንግዶችን እንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል፡፡ ክብርት ሚንስትር አያይዘውም መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት በዜጎች ላይ ጉዳት በአገር ላይ ደግሞ ስጋትን እያስከተለ በመሆኑ ኢትዮጵያም የዚህ ችግር ተጎጂ በመሆኗ በሰው የሚነግዱና ሰውን በማኅበራዊ ሚድያ ጭምር የተሳሳተ መረጃ በመስጠት እያታለሉ ወደ ውጪ በመላክ ወንጀል የሚሰሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ሁኔታውን እንዳባባሱት ገልፀዋል፡፡
አክለውም በህገ መንግስታችን እንዲሁም ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች መሠረት በሰዉ መነገድ ወይም በግድ ማሰራት የማይቻልና መከበር የሚገባው የሰው ልጆች መብት በመሆኑ በየትኛውም የአስተዳደደር እርከን ላይ የሚገኝ የፌዴራል እና የክልል ሕግ አውጪ፣ የዳኝነትና አስፈፃሚ አካላት ኃላፊነት በመሆኑ መንግሥት በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደረጃ የሚመራ ብሔራዊ ምክር ቤት መስርቶ በመሥራት ላይ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
መድረኩም የብሔራዊ ምክር ቤቱን የውስጥ አሠራር መመሪያ እንዲሁም መደበኛ ባልሆነ መንገድ ከአገር የሚወጡ ዜጎች ከመመለስ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት መዘጋጀቱን፤ በአጠቃላይ የበጀት ዓመቱን አፈፃፀም ገምግሞ የቅንጅታዊ ሥራዎችን ተጠያቂነት በተላበሰ አግባብ ለማስኬድ የሚያግዙ ማዕቀፎች የሚፀድቁበትና ቀጣይ አቅጣጫዎች የሚቀመጡበት መድረክ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በብሔራዊ የፍልሰት ምክር ቤት ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የፍልሰት ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በበኩላቸው ፍልሰት ተፈጥሮአዊና ሕጋዊ መብት ከመሆኑም በላይ ጠቀሜታው የጎላና ከሰው ልጅ የኑሮ ዑደት ጋር አብሮ የዘለቀና የሚኖር ነባራዊ እውነታ መሆኑን አውስተው፤ ኢትዮጵያ እንደ ፍልሰተኞች መነሻ አገርነቷ ዜጎችቻችን ለተሻለ ኑሮ ፍለጋና በሌሎች የተለያዩ ገፊና ሳቢ ምክንያቶች አገራቸውን ጥለው ወደተለያዩ አገራት ይፈልሳሉ፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች የአገራችንን እንዲሁም የመተላለፊያ ወይም የመዳረሻ አገራትን የፍልሰት ሕጎችና አሠራሮች ባልተከተለና መደበኛ ባልሆነ መንገድ የሚፈልሱ ሲሆን፤ ለዚህም የሰው ዝውውር መልማዮች፣ ደላሎችና አዘዋዋሪዎች ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ዜጎቻችን ለሞት፣ ለብዝበዛ፣ ለእንግልት እና ለሌሎች የከፉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች የሚዳረጉ ሲሆን፡ ለዚህ ችግር ዋና ተዋናይ የሆኑት የተደራጁ የወንጀል ቡድኖችም ቁሳዊ እና የገንዘብ ጥቅም ለማጋበስ በዜጎቻችን መብት፣ በሕዝባችን ክብር እና በአገር ደኅንነት ላይ ስጋት እየሆኑ በመምጣታቸው ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት በሰው የመነገድ እና ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀሎችን በመታገል ቀላል፣ መደበኛና ደህንነቱ የተረጋገጠ የውጭ አገር ስምሪትን በማስፋት የፍልሰተኞችን ሰብዓዊ መብቶችና ጥቅሞች ማስጠበቅ፣ የአገርን ደኅንነት ማረጋገጥ እንዲሁም የፍልሰትን እምቅ የልማት አቅም በአግባቡ መጠቀምን እንደሚጠይቅ አስገንዝበዋል፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚንስትሩ አክለውም ወቅቱ ፍልሰት ዓለም ዓቀፋዊ የሰብዓዊ መብት፣ የፖለቲካ፣ የጸጥታና የልማት አጀንዳ እንዲሁም የትብብር መስክ የሆነበት በመሆኑ፤ የፍልሰት መነሻ፣ መተላለፊያ እና መዳረሻ አገራትን የመልማት እድል በማስፋት ለ2030 የዘላቂ ልማት ግቦች መሳካት አዎንታዊ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ሲሆን፡ ከዚህም ሌላ የፍልሰት ጉዳይ የሰላምና ደኅንነት እንዲሁም የፖለቲካ እና ዲፕሎማሲ ፖሊሲዎችን ቅርጽና ሁኔታዎችን በመበየንም ላይ በመሆኑ የፍልሰት ፖሊሲዎች የፖለቲካ ፍላጎት ማስፈጸሚያ መሳሪያ፣ በልማት ለሚደረግ ትብብር እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚቀመጥ፣ ለቪዛ ዕቀባዎች በምክንያትነት የሚጠቀስ፣ ለሰብዓዊ ድጋፍ ቅነሳዎች እና የውጭ ዜጎችን በጅምላ ለማስወጣት ምክንያት እየሆነ መምጣቱን ለአብነት ጠቅሰው አስረድተዋል፡፡
ፍልሰት በአግባቡ ከተመራ ያድጋል የልማት እድልን ይፈጥራል ያሉት ክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሩ ለዚህም የአገራችንን ሉዓላዊነት፣ ደኅንነትና የመልማት ፍላጎት ከፍልሰተኞች ሰብዓዊ መብትና ክብር ጋር አመዛዝኖ መምራትን ስለሚጠይቅ የፍልሰትን ጉዳይ በአስር ዓመቱ የልማት እቅድ (2013-2022) እንዲካተት በመደረጉ የፍልሰት አሉታዊ ጎኖችን በመቀነስ አዎንታዊ ጎኖቹን በማጎልበት አገራችን እያካሄደች ከምትገኘው የኢኮኖሚ ሪፎርም ጋር አሰናስሎና አጣጥሞ ማስኬድ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል፡፡
አክለውም መደበኛ ያልሆነ ፍልሰትን መከላከል፣ ለወንጀል አጋላጭ ምክንያቶች ምላሽ መስጠት፣ የዳያስፖራ ተሳትፎን ማሳደግ፣ በተለያዩ አገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ዜጎቻችንን ደኅንነታቸውን እና ክብራቸውን በጠበቀ አኳኋን መመለስና በዘላቂነት ማቋቋም እንደሚገባ ገልፀው ከዚሁ ጋር በውጭ አገራት የሚገኙ ተጎጂን የመለየት፣ የማዳንና የመመለስ ጉዳይ የተጎጂዎች ድጋፍና ጥበቃ የሕግና የአሠራር ሥርዓቶችን ተከትሎ በቅንጅት ሊከናወን የሚገባና የአገራችንን ሰላምና ደኅንነት ከግምት ውስጥ ያስገባ ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡
በሰው የመነገድና ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን በመከላከል የተሻለ የፍልሰት አስተዳደር እንዲኖር ለማስቻል የተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶችን ማጽደቅን ጨምሮ ትብብርና ቅንጅት አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ የፌዴራልና የክልል የጥምረት ተቋማትን በመመስረት የተለያዩ ተግባራት በመከናወን ላይ ሲሆኑ በቀጣይነትም የጋራ ትብብሮችን በማጠናከር የፍልሰት ተጎጂዎችን ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረግ በሌላ በኩል የፍልሰት መነሻ የሆነውን ገፊ ምክንያት ድኅነትን፣ የሥራ ዕድል ውስንነትን ለመቅረፍ የሚከናወኑትን አገራዊ የልማትና የኢኮኖሚ ሪፎርሞች አጠናክሮ በመቀጠል፣ ሕጋዊ የውጭ አገር ሥራ ስምሪቱ በማስፋት ተደራሽ ማድረግ፣ ሕግ ማስከበርን በማጠናከር አጥፊዎችን ተጠያቂ ማድረግ፣ ለተመላሾች የተቀናጀ የመልሶ ማቋቋም ድጋፍን ማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራትን አፈፃፀም እየተከታተሉ ክፍተቶችን አስተካክሎ በቅንጅት መሥራት እንደሚያስፈልግ ገልፀው አመታዊ ስብሰባው በይፋ መከፈቱን አብስረዋል፡፡
ቀጥሎ የ2017 በጀት ዓመት በሰው የመነገድና ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን መከላከልና የፍልሰት አስተዳደር አገራዊ አፈፃፀም ረገድ የተከናወኑ ተግባራትን በሚመለከት የትብብር ጥምረት ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት ኃላፊ በአቶ አብረሀም አያሌው የትብብር ጥምረቱ በአመቱ ውስጥ ያከናወናቸው አበይት ተግባራትን፣ ያጋጠሙ ችግሮች እና የተሰጡ መፍትሄዎች የተካተቱበት ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በመጨረሻም ከፌዴራልና ክልል የመጡ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በየአካባቢያቸው ከፍልሰት ጋር ተያይዞ የሚያከናውኗቸውን ተግባራትና አጠቃላይ በፍልሰት ዙሪያ ያለውን አዝማሚያ በማንሳት አስተያየቶች ከቀረቡ በኋላ፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የፍልሰት ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እንዲሁም የፍትሕ ሚኒስቴር ሚንስትር ክብርት ወ/ሮ ሀና አርዓያስላሴ ቀጣይ የሚከናወኑ ሥራዎች አቅጣጫ ተሰጥተው የዕለቱ መድረክ ተጠናቋል፡፡