በሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት በሃዋሳ ከተማ ሲካሄድ የቆየው 6ኛው ዙር የፍትህ ሚኒስቴር እና የክልል ፍትህ ቢሮዎች የጋራ ጉባኤ መድረክ ተጠናቀቀ

The 6th Round Joint Conference Forum of the Ministry of Justice and Regional Justice Bureaus Held in Hawassa City, Sidama National Regional State, Concludes

በትላንትነው ዕለት ተጀምሮ የነበረው 6ኛው ዙር የፍትሕ ሚኒስቴር እና የክልል ፍትሕ ቢሮዎች የጋራ ጉባኤ መድረክ በዛሬው ዕለት የፌዴራል አስተዳደር ስነ-ሥርዓት አዋጅ አተገባበር ዳሰሳ እና የሴቶች፣ ህጻናትና ባለብዙ ዘርፍ ዳይሬክቶሬት የ2017 ዕቅድን አስመልክቶ ውይይት በማድረግ እንዲሁም የሀዋሳ ማዕከላዊ ማረሚያ ተቋምን በመጎብኘት ተጠናቋል፡፡

የአስተዳደር ስነስርዓት አዋጅ ጠቅላላ ዳሰሳ ፣ተቋማት ላይ የተደረጉ የክትትል ግኝቶች ፣የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የክለሳ ስነ-ስርዓት ላይ የታዩ ግኝቶች ፣ የታዩ መሻሻሎች እና የተለዩ ችግሮችን በፍትሕ ሚኒስቴር የፌደራል ህጎች ተፈፃሚነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሆኑት ወ/ት ሀወኒ ታደሰ አማካኝነት የቀረበ ሲሆን፣ ቀጥሎም በልዩ ትኩረት ለመብት ጥሰት ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ፍትሕ ማረጋገጥ ያስችል ዘንድ የሴቶች፣ ሕፃናትና ባለብዙ ዘርፍ ዳይሬክቶሬት የ2017 ዕቅድ በዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር ወ/ሮ ዳግማዊት አላምኔ አማካኝነት በመድረኩ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡

በኢፌዴሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር ኤርሚያስ የማነብርሀን (ዶክተር) በሁለቱም አቅራቢዎች የቀረቡትን ሰነዶች ተከትሎ የቀረቡት ሰነዶች ወሳኝ ጉዳዮች መሆናቸውን ገልፀው ጉዳዮቹ የህብረተሰቡን የዕለተ ዕለት ችግር ከመፍታት አንፃር ትልቅ ሚና እንዳላቸው እና መንግሥት በ2017 ዓ.ም ቁልፍ ጉዳይ አድርጎ ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡

አክለውም በተለይም የሴቶችና ሕፃናት ጉዳይ ቋሚ እና ተፈጥሯዊ ተግባራችን ስለሆነ ትኩረት ሰጥተን እንዲሁም የዘወትር ስራችን አድርገን መሥራት የግድ ነው ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታው የፍትሕ ሚኒስቴር መካከላኛ አመራሮች በጉባኤው እንዲገኙ ያስፈለገው ከአመለካት፣ አደረጃጀት፣ ከምርመራ፣ ከክስ እና ክርክር አንጻር እንደየስራ ክፍላቸው ለክልሎች ዕገዛና ድጋፍ በሚያስፈልጋቸው ወቅት የቅርብ ግንኙነት በመፍጠር ተገቢውን ድጋፍና ዕገዛ ለማድረግ ለማስቻል ነው፡፡

በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ተስፋዬ ዳባ በመድረክ ማጠቃለያ ንግራቸው እንደገለፁት በክልል ፍትሕ ቢሮዎች በኩል ያሉ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር ክልሎች የእርሰ በእርስ መልካም ተሞክሮ እንዲለዋወጡ እንዲሁም የፍትሕ ሚኒስቴር ለሁሉም ክልሎች አስፈላጊውን የትብብርና ድጋፍ ስራ እንደሚሰራ ገልፀው የአስተዳደር ስነሥርዓት አዋጅን አርቅቀው በምክር ቤቶቻቸው ያላፀደቁ ክልሎች በቀጣይ ዓመት ጉባኤ መድረክ በፊት አጸድቀው ወደ ስራ ማስገባት እንዳለባቸው በአፅንኦት አሳስበዋል፡፡

በቀጣይም በ2017 በጀት ዓመት የሚካሄደውን 7ኛው ዙር የፍትሕ ሚኒስቴር እና የክልል ፍትሕ ቢሮዎች የጋራ ጉባኤ ጉባኤ በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እንደሚያዘጋጅ ተመላክቷል፡፡

በጉባኤው ላይ የተባበሩት መንግስታት የምግብና መድሓኒት ቁጥጥር ቢሮ (UNODC) ተወካይ አቶ ኤርሚያስ ተቋማቸው ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር የሰራቸውንና በቀጣይ ሊሰራቸው ያሰባቸውን ተግባራት በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

በመጨረሻም የጉባኤው ተሳታፊዎች የሀዋሳ ማዕከላዊ ማረሚያ ተቋምን ጎብኝተዋል፡፡ በማረሚያ ተቋሙ በማረምና ማነፅ የሚሰጡ ልዩ ልዩ ትምህርትና ሥልጠና አገልግሎቶችን ማለትም በቀለም ትምህርት ፣በቴክኒክና ሙያ ፣ በግብርና ልማት ፣ በስነ ልቦና ፣ በማህበር አደደረጃጀት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በመጎብኘት እና የአርንጓዴ አሻራ መርሀ-ግብር ችግኝ ተከላ በማካሄድ የጉባኤው መድረክ ተጠናቋል፡፡

Tagged Under: administrative bureaus Capacity Building Children's Rights civil liberties conference correctional services Criminal Justice enforcement federal justice system fundamental rights hawassa Human Rights joint Justice law Legal Reform National prison prison reform Regional Regional Justice Bureaus sidama sidama national regional state state UNODC Women's Rights
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች