
ክቡር አቶ ተስፋዬ ዳባ ላለፉት ሃያ ዓመታት በተለያዩ መንግስት ኃላፊነት ቦታዎች ተሹመው አገራቸውን በማገልገል በአገሪቱ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፣ የፍትህ ስርዓት እንዲጎለበት እና አገሪቱ ከሌሎች አገራት ጋር ያላት ግንኙነት እንዲጠናከር የራሳቸው የጎላ ድርሻ ተወጥተዋል እየተወጡም ይገኛሉ፡፡
ክቡር አቶ ተስፋዬ ዳባ ተሹመው ከሰሩባቸው ተቋማት መካከል በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ደኤታ፣ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የውጭ ግንኑነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የፍትሕ ቢሮ ም/ኃላፊ፣ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የካቢኔና የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክተር፣ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የፕሬዝደንት አማካሪ እና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፍትሕ አካላት ባለሞያዎች ስልጠና ማዕከል የጥናትና ፕሮጀክት ዝግጅት ዲፓርትመንት ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል፡፡
– ክቡር አቶ ተስፋዬ ዳባ የተለያዩ ተቋማትን በኃላፊነት በመሩበት ወቅት ሀገራችን ከሌሎች አገራት ጋር ያላት ግንኙነት እንዲጠናከር፣ የፍትህ ስርዓት እንዲሻሻል፣ አዲስ ህጎች እንዲወጡና መሻሻል የሚገባቸው ነባር ህጎች እንዲሻሻሉ፣ የፍትህ ተቋማት በአሰራር፣ በአደረጃጀት፣ ብቃት ባላቸው ባለሞያዎችና በዘመነዊ ቴክኖሎጂ መሳሪያዎች በተገቢው ሁኔታ እንዲደራጁ ጠንካራ ስራዎችን ሰርተዋል፡፡
– ክቡር አቶ ተስፋዬ ዳባ በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስቴር ደኤታ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙ ሲሆን ሕገ መንግስቱን እና ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን እንዲጠበቅ፤ የሕግ የበላይነትን እንዲረጋገጥ፤ ወንጀል የፈፀሙ ግለሰቦች ተጠያቂ እንዲሆኑ፣ የወንጀል ሕግ እንዲከበር፤ በተለያዩ ወንጀሎች የተመዘበሩ የሕዝብና የመንግስት ሐብቶች እንዲመለሱ በማድረግ የሕዝብና የመንግስት ጥቅም እንዲጠበቅ የተለያዩ ስራዎች በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡