የኢ.ፌ.ደ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ከወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በአማራ ክልል 8 የባህል ፍርድ ቤቶችን ለማጠናከር የሚያግዙና ለቢሮ አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ ቁሳቁሶች ድጋፍ ሚያዝያ 20/2018 ዓ.ም አድርጓል፡፡
የድጋፉ ርክክብ የፍትሕ ሚኒስቴር ከክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ከወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር በክልሉ በባህል ፍርድ ቤቶት ለሚያገለግሉ ሽማግሌዎች አቅም ግንባታን ለማጠናከር በማለም ከሚያዝያ 20-21/2018 ዓ.ም ባዘጋጁት የስልጠና መድረክ ላይ ተደርጓል፡፡
በዚህ ወቅት እንደተገለፀው በፍትሕ ሚኒስቴር የሶስት ዓመቱን የፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድን ውጤታማ ለማድረግ ከተሰሩ ስራዎች መካከል የመሰረተ-ማህበረሰብ ፍትሕ አንዱ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፤ በዚህም የባህላዊ እና መደበኛ የፍትሕ ሥርዓትን ተመጋጋቢ ለማድረግ የባህላዊ ፍርድ ቤቶች እና ሌሎች የማህበረሰብ ፍትሕ አገልግሎት መስጫ ዘዴዎችን ተደራሽ የማድረግ እና ህጋዊ ዕውቅና የመስጠት ሥራዎች በተለያዩ ክልሎች መከናወናቸው ተወስቷል፡፡
ባሁኑ ወቅትም 8 ክልሎች እና አንድ የከተማ አስተዳድር ህግ በማውጣት ወደ ትግበራ የገቡ ሲሆን፤ከዚህ ቀደም ተገቢው ዕውቅና ሳይሰጣቸው አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ ባህላዊ የፍትሕ ሥርዓቶችን ለማስፋት የታቀደውን የመሰረተ-ማህበረሰብ ፍትህ ፍኖተ ካርታን ተግባራዊ ማድረግ መቻሉ ታውቋል፡፡
በቀጣይም በፍትሕ ሚኒስቴር በኩል ለክልሉ የባህል ፍርድ ቤቶች የአቅም ግንባታን ጨምሮ በተለያየ መልኩ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተጠቁሟል፡፡
በተያያዘም በአማራ ክልል የህግና ፍትሕ ኢኒስትቲውት እንዲሁም በከተማው አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉ የባህል ፍርድ ቤቶች ጉብኝት ተደርጓል፡፡
በመድረኩ የፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታን ጨምሮ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት፤የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ሃላፊ፤ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ጠቅላይ መምሪያ ም/ኮሚሽነር፤ የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ተወካይ፤ የባህል ፍርድ ቤት ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡