አዲሱን የንብረት ማስመልስ አዋጅ ቁጥር 1364/2017 አስመልክቶ የፓናል ዉይይት ተካሄደ

Panel Discussion Held on the New Asset Recovery Proclamation No. 1364/2017

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት አሰተባባሪነት ምንጩ ያልታወቀ ሀብትን ለማስመለስ የወጣዉን አዲሱን አዋጅ ቁጥር1364/2017 አስመልክቶ ዛሬ ሚያዚያ 9 ቀን 2017 ዓ.ም የተቋሙን መካከለኛ አመራሮች እና ባለሙያዎች ያሳተፈ የአንድ ቀን የፓናል ዉይይት በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

በፓናል ዉይይቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የተቋም ግንባታ እና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ ክቡር ኤርምያስ የማነብርሃን ( ዶ/ር)፣ ዉይይቱ ያስፈለገበት ዋናዉ ምክንያት አዋጅ ቁጥር 1364/2017 ለፍትሕ ሚኒስቴር ግንባር ቀደሙ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ስርአቱን ትራንስፎርም ለማድረግ በ 3 ዓመት ፍኖተ ካርታው ከተካተቱ የሕግ ማሻሻያ ስራዎች ውስጥ አንዱ በመሆኑ እና በዜጎች መካከል ያለዉን ፍትሃዊና ሚዛናዊ ግንኙነት ለማስተካከል ትልቅ ሚና የሚጫወት ሕግ መሆኑን ጠቅሰው ዉይይቱ ከጉዳዩ ዋነኛ አስፈጻሚዎች ጋር መደረጉ ጠቀሜታዉ የጎላ እንደሆነም አያይዘዉ ገልጸዋል፡፡

ከተባበሩት መንግስታት የአደንዛዥ ዕፅ እና የወንጀል ጉዳዮች ቢሮ የኢትዮጵያ ዋና መሥሪያ ቤትን ወክለዉ በፓናል ዉይይቱ ላይ የተገኙት አቶ አብርሃም አያሌዉ በበኩላቸዉ የኢትዮጵያ መንግሥት የሀብት ማስመለስ ስራዉን ሲሰራ የዳሰሳ ጥናት በማድረግና የአቅም ግንባታ ስራዎችን በመሥራት እገዛ ሲያደርግ እንደቆየ ገልጸዉ ወደፊትም እገዛዉ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

ሀብት ማስመለስ ዋና ዓላማዉ ወንጀልን በመከላከል ተጠያቂነትን ማረጋገጥ በመሆኑ በሂደቱ ላይ የሚያጋጥሙ የመረጃ ክፍተቶችን ለመሙላት ከተለያዩ ተቋማት ጋር ተቀራርቦ መሥራት፤ የምርመራ እና የአደረጃጀት ስርአታችንን ማጠናከር ላይ አዲሱ የሀብት ማስመለስ ሕግ በቂ ምላሽ የሚሰጥና ከዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች ጋር በመናበብ የሚዘረፈዉን እና ከሀገር የሚሸሸዉን ሀብት መዳረሻ ሀገሮችን አዉቀን ንብረት ማስያዝ፤ ማስመልስ እና አጠቃላይ የምርመራዉን ስራ በጋራ መሥራት የተሻለ ዉጤት እንደሚኖረዉ የሕግ ጥናት፤ ማርቀቅ፤ማረምና ማጠቃለል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ አዲስ ጌትነት አመላክተዋል፡፡

በዉይይቱ ላይ በተለይም አዋጅ ቁጥር 1178/2012 የንብረት መወረስ ድንጋጌ በግልጽ ካልተደነገገ ንብረት የማይወረስ ስለመሆኑ በወንጀል ህጉ መደንገጉ የፈጠረዉ ክፍተት እንደነበረና ልዩ የምርመራ ዘዴን መጠቀም አለመቻል፤ የጥቆማ አቀባበል ችግር፤ የምርመራ ቡድን አለማዋቀር፤ የስራ ክፍሎች አለመናበብ እና የሚና መደራረብ በጉልህ የታዩ ዉስጣዊ ተግዳሮቶች ሲሆኑ፣ የባንኮች የሚስጥራዊነት መርህ፤ መረጃን ለደንበኞች አሳልፎ መስጠትና የመረጃ ሰጭ አካላት ትኩረት ማነስ ተጨማሪ ዉጫዊ ተግዳሮቶች እንደነበሩ በዉይይቱ ላይ ተገልጹዋል፡፡

በዉይይቱ ላይ ሀገራት የተለያየ የሀብት ማስመለስ ልምድ ያላቸዉ ሲሆን በተለይ ከበደቡብ አፍሪካ እና በዩናይትድ ኪንግደም የተወሰዱ ልምዶች ላይ ሰፊ ዉይይት የተካሄደ ሲሆን ሀገራቱ የሀብት ማስመለስ ህጎችን ሲያወጡ መሠረታዊ የሆኑ የግለሰቦች መብትን እንዳይነካ የመብት ጥበቃ ዘዴዎችን አብረዉ ከመደንገግ ጀምሮ በፓርላማዎቻቸዉ ኮሚቴዎችን እስከ ማቋቋም እንደደረሱ ተገልጸዋል፡፡

የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ቴዎድሮስ ሳሙኤል በበኩላቸዉ አዲሱን አዋጅ ማዉጣት ያስፈለገዉ እስካሁን በተለያዩ ህጎች ዉስጥ ተበታትነዉ ያሉትን የንብረት ማስመለስ ድንጋጌዎችን በአንድ ወጥ ሕግ ዉስጥ በማካተት ለአፈጻጸም ምቹ የሆነ ሥርዓት በማስፈለጉ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በመጨረሻም ከተሳታፊዎች ለተነሱ ሀሳብ አሰተያየቶች እንዲሁም ጥያቄዎች በአርቃቂ ቡድኑ ምላሽ ተሰጥቶባቸው የፓናል ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

Tagged Under: 1364/2017 Anti-Corruption asset asset forfeiture Asset Recovery Capacity Building civil liberties confiscation criminal criminal justice reform democratic Discussion Due Process FDRE federal federal democratic republic of ethiopia (fdre) Financial Crimes fundamental rights Human Rights International Cooperation Legal Reform Money Laundering panel panel discussion proclamation proclamation no. 1364/2017 recovery republic
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች