
አቶ አዲስ ጌትነት ከሐምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ሶስት ዓመታት በምክትል ዳይሬክተር ጀነራልነት ከዛም በኋላ እስከአሁን ድረስ ባሉት ዓመታት በዳይሬክተር ጀነራልነት የሕግ ጥናት፣ማርቀቅ እና ማጠቃለል ዳይሬክቶሬት ጀነራልን እየመሩ ሲሆን የሥራ ክፍሉን በመምራት ለፖሊሲ ሕግና ስትራቴጂ ግብዓት የሆኑ ጥናቶችን በበላይነት መርተዋል፤ ከፍተኛ ሀገራዊ ፋይዳያላቸውን የሕግ ማዕቀፎች በማዘጋጀት ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፣ መርተዋል፣ የመንግስት ተቋማት የሚያዘጋጇቸውን የፖሊሲ እና የሕግ ማዕቀፎች ጥራታቸውን እንዲጠብቁ በማድረግ፣ ተቋማቱን በማገዝ ጉልህ ሀገራዊ አበርክቶ አላቸው። ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎም ሪፎርም የተደረጉ የሕግ እና የፖሊሲ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ አሁንም ኃላፊነታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ በመወጣት ተቋሙ እንደሀገር የተጣለበትን ኃላፊነት ረገድ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል። በእርሱ አመራር የሥራ ክፍሉ በተሳካ ሁኔታ የሕግ ማዕቀፎችን በመፈተሽ እና በማዘመን ከዓለምዓቀፍ ስታንዳርድ እና ከኢትዮጵያ የእድገት ግብ ጋር የተናበቡ እንዲሆኑ አስችሏል። አቶ አዲስ በማስተባበር ክህሎታቸው፣ በየትኛውም ደረጃ ከሚገኙ ባለድርሻ እና አጋር አካላት ጋር አብሮ በመስራት የተጠቃለለ እና ሁሉን አካታች የሆነ ፖሊሲ በመቅረጽ ስኬታማ ናቸው። በኃላፊነት ከመመደባቸው በፊትም በተለያዩ የዐቃቤ ሕግነት ደረጃዎች ተመድበው በወንጀል ምርመራና ክስ ሥራቸው ጥራትና ብቃት የተመሰከረላቸው ነበር። አዲስ ከ15 ዓመት በላይ ያካበታቸውን የሥራ ልምድ በመጠቀም ፍትሕን ለማስፈን እና እኩልነትን ለማረጋገጥ ብቁ የሆነ የሕግ ማርቀቅ እና የፖሊሲ ዝግጅት ኃላፊነቱን ለመወጣት ዝግጁ ነው፡፡