በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ በክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ የተመራ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የትራንስፎርሜሽን እቅድ ግብረ ኃይል አባላት በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሀዋሳ ከተማ በመገኘት ከክልሉ የፍትሕ አካላት አብይ ኮሚቴ ጋር በሶስት አመቱ የፍትሕ አካላት ትራንስፎርሜሽን እቅድ የክልሉን የሁለት አመታት አፈጻፀም ሰኔ 19/2017 ዓ.ም በጥልቀት ገምግሟል።
ግምገማው የተጀመረው በክልሉ በቀረበው የሁለት አመታት የትራንስፎርሜሽን እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ሲሆን፤ በሪፖርቱ ላይ በክልሉ በማኅበረሰብ አቀፍ ፍትሕ አገልግሎት የተገኙ ስኬቶችን፣ የክልሉን ፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ ለመደገፍ የተደረጉ ጥረቶችና የተመዘገቡ ውጤቶች፣ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር በተለይም የመዛግብት ውዝፍ ለማጥራት የተወሰዱ እርምጃዎች፣ ወንጀልን ለመከላከል በCCTV ካሜራ በመጠቀም የተመዘገቡ ስኬቶች፣ የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕግን ከማውጣት ጀምሮ እስከ ትግበራ ድረስ የተገኙ ውጤቶች፣ በሕዝብና መንግሥት ጥቅም ለማስከበር የተደረጉ ጥረቶች፣ በክልሉ ፍትሕን ተደራሽ ለማድረግ ሕዝብን በማሳተፍ በተለይ በፖሊስ ኮሚሽን በኩል የተሰሩ ስራዎች እና የተገኙ ስኬቶች፣ ታራሚዎችን ከማረምና ከማነፅ አንጻር እንዲሁም የታራሚዎችን የሰብዓዊ መብት አያያዝ በማሻሻል ረገድ የተሰሩ ስራዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በሪፖርቱ ላይ የተደረገውን ውይይት ተከትሎ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው እና የፍትሕ ሚኒስቴር የትራንስፎርሜሽን እቅድ ግብረ ኃይል አባላት አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን አቅርበው ከክልሉ ምክር ቤት፣ ፍትሕ ቢሮ፣ ፖሊስ ኮሚሽን እና ማረሚያ ቤት ኮሚሽን በኩል ማብራሪያ ተሰጥቶበታል።
በዚህ መሠረት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በሁለት አመቱ ትግበራ ወቅት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልፀው በቀሪው የእቅዱ ትግበራ ጊዜ ትኩረት ተደርጎባቸው ሊሰሩ የሚገባቸው ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ ሰጥተዋል። በዚህ መሠረት የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕግን በማስተግበር የህዝቡን የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ጥያቄዎችን ከመሰረቱ ለመቅረፍ በትኩረት መሰራት እንዳለበት፤ የፍትሕ ባለሙያዎችና አመራር ከማጥራት አንፃር የተጀመሩ ስራዎችን በትራንስፎርሜሽን አቅዱ በተመላከተው መሠረት አጠናክሮ መተግበር እንዳለበት፤ የፍትሕ አገልግሎቱን ተደራሽ ከማድረግና በቴክኖሎጂ በመደገፍ ረገድ የተጀመሩ ስራዎችን በተገቢው ትኩረት ማስቀጠል እንደሚገባ፣ በክልሉ ምክር ቤት በኩል ቀሪ ስራዎችን በመገምገም በቀረው ጊዜ ገደብ ውስጥ ተገቢ ክትትልና ድጋፍ እንዲደረግ አንስተው በፍትሕ ሚኒስቴር በኩልም ምርጥ ተሞክሮ ሊሆኑ የሚችሉትን ስራዎች ለማካፈል ጥረት እንደሚደረግ ገልፀዋል።
በመጨረሻም የተጀመረውን የክልሉን የትራንስፎርሜሽን እቅድ ትግበራ ለመደገፍ የኮምፒውተር ድጋፍ በማበርከት በፍትሕ ሚኒስቴር ደረጃ የተዘጋጁትን የታክስና ጉምሩክ ወንጀሎች እንዲሁም በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ምርመራ፣ ክስ እና የችሎት ማስገንዘቢያ መጽሑፍት (Handbook) ለክልሉ ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አስረክበዋል።