በፍልሰት ዙሪያ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የጋራ ፎረም ሊመሰርቱ ነው

NGOs Working on Migration to Form Joint Forum

በፍልሰት ዙሪያ የሚሰሩ ዓለም አቀፍና አህጉራዊ ድርጅቶችን ጨምሮ መንግስታዊ ያልሆኑ አጋሮች እና የመንግሥት ተቋማት ቅንጅታዊ አሠራርን ለመፍጠር እና አገር አቀፍ ፎረም ስለሚመሠረትበት ሁኔታ የሚመክር የውይይት መድረክ ሚያዚያ 03 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ በራዲሰን ብሉ ሆቴል ተካሂዷል፡፡

የምክክር መድረኩ በዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት (IOM) የፋይናንስ ድጋፍ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት አማካኝነት የተዘጋጀ ሲሆን ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ የሆኑ አጋር ድርጅቶች እና የመንግሥት ተቋማት ተወካዮች ተሳትፈውበታል፡፡

መድረኩን በንግግር የከፈቱት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብርሀም አያሌው በፍልሰት አስተዳደር ውስጥ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም የዓለም አቀፍ ተቋማት ትብብርና ቅንጅት አስፈላጊ መሆኑን በአጽንኦት አንስተዋል፡፡

ፍልሰትን በአግባቡ ለማስተዳደር በተለይም በሰዎች መነገድና ሰዎችን በህገ-ወጥ መንገድ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1178/2012 መሠረት በፍትሕ ሚኒስቴር የሚመራ ብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ተቋቁሞ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ ያሉት ኃላፊው ከእነዚህ ተግባራት ውስጥም በፍልሰት አስተዳደር ውስጥ ተዋንያን የሆኑ አካላት በመካከላቸው ያለው ቅንጅት እንዲጠናከር ማድረግ፣ የተግባራት ድግግሞሽን ሊያስቀሩ የሚችሉ የግንኙነት መድረኮችን መፍጠር እንዲሁም መንግሥት ከሚያወጣቸው መሠረታዊ አቅጣጫዎች አንፃር የመንግሥትን ፍላጎት መሠረት ያደረገ ፕሮጀክት ቀርፀው እንዲንቀሳቀሱ እና በተበታተነ መልኩ ያለውን ስራ በትብብር እና በአጋርነት ወደ አንድ ላይ አቅምን አሰባስቦ መደበኛ ያልሆነውን ፍልሰት በመቀነስ ረገድ ሁላችንም የድርሻችንን እንድንወጣ ለማድረግ ይህ የምክክር መድረክ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

በመቀጠልም በሀገራችን የፍልሰት አስተዳደር ዙሪያ በመንግሥትና እና መንግስታዊ ባልሆኑ አጋሮች እንዲሁም መንግስታዊ ባልሆኑ አጋሮች እርስ በርሳቸው መካከል ያሉት ቅንጅቶች፣ ክፍተቶች እና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ መነሻ ጽሑፍ በብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም አማካኝነት የቀረበ ሲሆን የዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት (IOM) እና የጀርመን የልማት ተራድኦ ድርጅት (GIZ) ተወካዮችም መንግስታዊ ባልሆኑ አጋሮች መካከል ስላሉ ልምዶቻቸውን አጋርተዋል፡፡

ይህንን ተከትሎም በተሳታፊዎች ውይይት ከተደረገ በኋላ በመንግሥት በኩል እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በተቀናጀ መንገድ ለማገዝ መንግስታዊ ያልሆኑ አጋር አካላት ፎረም አስፈላጊ መሆኑ ስምምነት ላይ ተደርሶ ፎረሙ የሚፈጠርበትን ሁኔታና ተግባራዊ ስለሚሆንበት አግባብ ከሌሎች አገሮችና ከተለያዩ መሰል ፎረሞች ልምድ በመቀመር በቀጣይ ሀገር አቀፍ ፎረሙን ለመመስረት ለሚዘጋጀው መድረክ የመነሻ ጽሁፍ የሚያቀርብ ከመንግሥትና ከአጋሮች የተውጣጣና ስምንት አባላት ያሉት ቴክኒካል ኮሚቴ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡

Tagged Under: addis ababa Collaboration Coordination cross-border migration development cooperation Forum german development cooperation (giz) Human Trafficking international international organization for migration (iom) iom Irregular migration management Migration migration governance Migration Management ministry ministry of justice (ethiopia) National national migration coordination unit ngo organization policy coordination Stakeholder Engagement technical committee unit
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች