የኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሥራ ሃላፊዎችና ሠራተኞች የ2018 ዓ.ም የክረምት አረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ተከትሎ «ተስፋን እንትከል» በሚል መሪ ቃል በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 (ቦሌ ቪ.አይ.ፒ ፓርክ) በመገኘት ከ5,000 በላይ ችግኞችን ተክለዋል።
በተከላው ላይ ለጥላ፣ ለምግብነትና ለአካባቢ ጥበቃ የሚሆኑ ሀገር በቀል የችግኝ ዝርያዎች የተተከሉ ሲሆን፣ ይህ በአገር አቀፍ ደረጃ በተመሳሳይ ቀን እየተከናወነ ያለው የአንድ ጀምበር 800 ሚሊዮን የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አገራችን በፅናት የያዘችውን የአረንጓዴ አሻራ ራዕይና ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው።
በዕለቱ እንደተገለጸው፣ የችግኝ ተከላው በዓለም ዓቀፍ ደረጃ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለመቀነስ የሚያበረክተው ሚና ከፍተኛ ነው። ከተከላው ጎን ለጎን የተተከሉት ችግኞች እንዲፀድቁና እንዲያድጉ አስፈላጊው ተከታታይ ክትትል የሚደረግላቸው ሲሆን፤ በዕለቱ የተስተዋለው በጋራ የመሥራት ባህልና አገራዊ ተነሳሽነት በየተሰማራንበት የሥራ መስክ ሁሉ እንደ መልካም ተምሳሌት ተወስዶ በላቀ ደረጃ ሊደገምና ሊጎለብት እንደሚገባ መልእክት ተላልፏል።