የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የ2018 በጀት ዓመት አመታዊ የስራ አፈፃፀም ሪፖርት እና የ2019 ዓ.ም የበጀት ዓመት ዕቅድ ላይ የተቋሙ ከፍተኛና መካከለኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ዉይይት አደረገ፡፡
በሪፖርቱ እንደተመላከተው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ፣ የወንጀል ሕጉን ከማስከበር፣ እንዲሁም የፌዴራል መንግስቱንና የሕዝብን ጥቅም ከማስጠበቅና ፍትሕን ከማስፈን አንፃር በበጀት አመቱ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉ ተገልጿል።
ለአብነትም ለረዥም ዓመታት የቆየው የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ የፀደቀበትና የቅድመ-ትግበራ እንቅስቃዎች የተጀመሩበት፣ ለፍትሕ አዲስ መሰረት ለመጣል የሚያስችል ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ተነድፎ ትግበራ የተጀመረበትና አዲስ መዋቅር የተዘረጋበት፣ የዓለም ዓቀፍ ድርድር ስኬታማነት የጨመረበት፣ በስልጠና ረገድ ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበበት፣ ከፖሊስ ጋር የምርመራና የክስ ስራዎችን አብሮ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈርሞ ስራ የተጀመረበትና ውጤት የተመዘገበበት ዓመት መሆኑ ተጠቁሟል።
በተያያዘ ማኅበረሰብ አቀፍ የፍትሕ አገልግሎቶችን በማስፋፋት ፣ የባህላዊ ፍርድ ቤቶችን ሰብዓዊ መብት ተኮር አሠራር በማጠናከር፣ የነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎትን ተደራሽ በማደረግ፣ የሕግ ግንዛቤ በማሳደግ፣ እና የጥብቅና ፈቃድ አሰጣጥና እድሳት ሥርዓትን በማዘመን፣ እንዲሁም የሙያ ሥነ-ምግባር ተጠያቂነትን በማስፈን ረገድ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸዉ ተመላክቷል፡፡ በተጨማሪም በወንጀል ምርመራና ክስ አፈፃፀም በተለይም የምርመራ መዝገቦች የማጥራትና የማስቀጣት ምጣኔ እንዲሁም የሴቶችና ሕፃናት ጉዳዮች አፈፃፀም እና የሀብት ማስመለስ ተግባራትን በተመለከተ አበረታች ዉጤቶች መመዝገባቸዉ ተገልፆል፡:
በተጨማሪም በፍትሐብሔር ጥቅም ጥበቃ፣ በዓለም አቀፍ ግልግል ዳኝነት፣ በድርድር አፈታት፣ በውል ምርመራና የሕግ ምክር አገልግሎቶች እንዲሁም በሰነድ ማረጋገጥና ምዝገባ ዘርፎች ከፍተኛ ውጤቶች የተመዘገቡ ሲሆን በተለይም የመንግስትን የገንዘብ ጥቅም በማስጠበቅና ያላግባብ የሚወጡ ወጪዎችን በመቀነስ ረገድ ተጨባጭ ውጤቶች ተገኝተዋል።
በሕግ ጥናት፣ በሕግ ማርቀቅና ምክር እንዲሁም በሕግ ምርመራና እርማት ዘርፎች የተከናወኑ ሥራዎችም በአገሪቱ የሕግ ሥርዓት ጥራትን ለማሳደግ፣ የሕግ ማሻሻያን በጥናታዊ መሠረት ለመምራት እና ወቅታዊ፣ ተግባራዊ እና የተቀናጀ የሕግ ማዕቀፍ ለመገንባት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ተመላክቷል።
በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ የዲጂታል ሽግግር ተግባራት በተመለከተም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን የመረጃ አያያዝ ሥርዓት በማዘመን፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍናን በማሳደግ የተጠያቂነትና የግልጽነት ደረጃን በማጠናከር እንዱሁም በመረጃ የተደገፈ የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል መሠረት መጣል መቻሉ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴር በ2018 ዓ.ም ያስመዘገባቸውን ስኬቶች አጠናክሮና አዳዲስ ተግባራትን ጨምሮ ለ2019 የበጀት ዓመት ዕቅድ የተዘጋጀ ሲሆን በተለይም የሽግግር ፍትሕ ትግበራ የሚጀመርበት፣ የማሕበረሰብ ፍትሕ፣አማራጭ የሙግት መፍቻ፣ ትብብርና ቅንጅት፣ የቅድመ ምርመራ ስራ ተጠናክሮ የሚቀጥልበት፣ አዲስ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የሚጀመርበት፣ የወንጀል ሥነ-ሥርዓትና የማስረጃ ሕጉ የሚተገበርበትና ሌሎች ዘርፈ ብዙና ሰፋፊ ተግባራት የሚፈፀሙበት የበጀት ዓመት መሆኑ ተገልፆል።