በየዓመቱ ሐምሌ 23 ቀን የሚከበረው በሰው የመነገድ ወንጀል መከላከል ቀን በዛሬው ዕለት በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ13ኛ ጊዜ ተከብሮ የዋለ ሲሆን የፍትሕ ሚኒስቴር ከአለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) ጋር በመተባበር በሀገራችን ለ2ኛ ጊዜ “በማጭበርበር መረብ ውስጥ የወደቁ የግዳጅ ወንጀል ሰለባዎች” (Trapped Behind the Scam) በሚል መሪ ቃል በፓናል ውይይት ተከብሯል፡፡
በፓናል ውይይቱም የኢትዮጵያ መንግስት በሰዎች የመነገድና ተጎጂዎችን ለግዳጅ ወንጀል የመዳረግ ድርጊትን ለመከላከል በርካታ ተግባራትን እያከናወነ እንደሚገኝ የተገለፀ ሲሆን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመራ ብሔራዊ የትብብር ጥምረት ምክር ቤት በማቋቋም ፣ጠንካራ የሕግ ማዕቀፎችን በማውጣት፣ በተጎጂዎች ጥበቃና መልሶ ማቋቋም፣ በግንዛቤ ፈጠራ፣የሕግ ተጠያቂነትን በማረጋገጥ እና በሌሎች ተግባራት ዓለም ዓቀፍ ትብብሮችን በማጠናከር ሰፊ የሆነ ብሔራዊ ምላሽ እየሰጠች እንደምትገኝ ተመላክቷል፡፡
በተጨማሪም ከ2019-2023 ዓ.ም የሚተገበር ሀገራዊ የተቀናጀ የፍልሰት አስተዳደር ስትራቴጂክ ረቂቅ እቅድ መዘጋጀቱ የተገለፀ ሲሆን እቅዱ በዋናነት በሰው የመነገድ ወንጀል መከላከልን፣ ህጋዊና መደበኛ የፍልሰት መንገዶችን፣ የድንበር አስተዳደር፣ የተጎጂዎች ጥበቃን፣የመረጃ አሰባሰብና እንዲሁም ለሀገራዊና ዓለም አቀፍ ትብብርና ቅንጅታዊ ምላሽ አስጣጥ ልዩ ትኩረት የሰጠ እንደሆነ ተገልፆል።
በስዎች መነገድና ሰዎችን ለግዳጅ ወንጀል የመዳረግ ወንጀሎች የተማሩ ሰዎችን ጭምር በተለያዩ ማስታወቂያዎች በማባባልና ቴክኖሎጂን በመጠቀም የሚፈፀሙ መሆናቸው የተገለፀ ሲሆን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደ ማይናማር፣ ካምቦዲያና ላኦስ ባሉ የደቡብ ምስራቅ ኤዥያ አገራት በሕገ-ወጥ መንገድ ተወስደው በኮምፒውተር ማጭበርበርና በሳይበር ወንጀሎች ላይ በግዳጅ እንዲሰማሩ የተደረጉ ዜጎችን ለመታደግ ልዩ ኮሚቴ በማቋቋም ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የተቋማትን ኃላፊነት በተመለከተ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ከኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት፣ ከዓለም አቀፋ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) እና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት አደንዛዥ ዕጽና ወንጀል መከላከል ቢሮ (UNODC) የተዉጣጡ የሥራ ኃላፊዎች የተሳተፉበት ሰፋ ያለ የፓናል ውይይት የተካሄደ ሲሆን በጥቅሉ ወንጀሉን ለመከላከል ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታቸውን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በማጠናከርበትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ አፅንኦት ተሰጥቷል፡፡ በዚህ የፓናል ውይይት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ የመንግስት ተቋማት ተወካዮች፣ የዲፕሎማቲክ ተወካዮች፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተቋማት ተወካዮች የዩናይትድ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የግል የልማት ድርጅቶች፣ የሚዲያ ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ነበሩ፡፡