የፍልሰት ምርምርን ለማጠናከር ያለመ የመግባቢያ ስምምነት ተፈረመ

Memorandum of Understanding Signed to Strengthen Migration Research

በብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት የፍልሰት ምርምር የሥራ ቡድን መሪ የሆነው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የትምህርት ሚኒስቴር ሶሊሲቲ (Coli*City Initiative) እና ዴዚም (German Centre for Integration and Migration Research/DEZIM) ከተባሉ ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር የፍልሰት ምርምርን ለማጠናከር የሚያግዝ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ፡፡

የፊርማ ስነ-ስርዓቱን በንግግር ያስጀመሩት የትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ኮራ ጡሹኔ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች መደበኛ ባልሆኑ የፍልሰት መንገዶች ከአገር በመውጣት ለከፍተኛ የመብት ጥሰትና ለብዝበዛ እየተጋለጡ ሲሆን፤ ለሞት አደጋ እየተጋለጡ የሚገኙትም በርካቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ መንግሥት በአንድ በኩል ወንጀሎቹን ለመከላከል ሰፋፊ ስራዎችን እያከናወነ ሲሆን፤ በተጨማሪም ሕጋዊ የውጭ አገር ሥራ ስምሪትን ለማስፋት በርካታ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል፡፡ ይሁንና መደበኛ ባልሆነ መንገድ ወደ ውጭ አገራት የሚፈልሱት ዜጎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሆኑ ችግሩ እየተባባሰ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም የፍልሰት ገፊ ምክንያቶችን እና ሊወሰዱ የሚገባቸው መፍትሄዎች በተቀናጀ መልኩ ለይተው የሚያስቀምጡና በሳይንሳዊ ማስረጃ ላይ የተመሰረቱ ምርምሮች ሊካሄዱ እንደሚገባ የተናገሩት ክቡር አቶ ኮራ፤ ለዚህም በብሔራዊ የትብብር ጥምረት ስር የተቋቋመውን የፍልሰት ምርምር የሥራ ቡድን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡ የስራ ቡድኑን የማስተባበር ሕጋዊ ኃላፊነት የተሰጠው የትምህርት ሚኒስቴርም የመሪነት ሚናውን ለመወጣት ከመቼውም ጊዜ በላይ በትጋት እንደሚንቀሳቀስ ገልጸው፤ የፍልሰት ምርምርን ለማገዝ የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነትም የዚሁ ጥረት አንዱ አካል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

መቀመጫውን ካናዳ ያደረገው የሶሊ ሲቲ ተወካይ ፕሮፌሰር ሃራልድ ቦርደር እና የጀርመኑ የምርምር ተቋም ዴዚም ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶክተር ኖዓ ሃ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የፍልሰት አስተዳደር ውስጥ በምርምር ሊመለሱ የሚያስፈልጉ እና ሳይንሳዊ መረጃና ማስረጃ ሊቀርብባቸው የሚያስፈልጉ በርካታ ስትራቴጂክ ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ለዚህም ተቋሞቻቸው የትምህርት ሚኒስቴርንና የአገሪቱን ዩኒቨርሲቲዎች ለማገዝ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

በፊርማ ስነ ሥርዓት መድረኩ ላይ በትምህርት ሚኒስቴር የምርምርና ማኅበረሰብ ተሳትፎ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሰራዊት ሃንሺሶ የፍልሰት ምርምር የሥራ ቡድን ሚናን እንዲሁም የተቋማቸውን ኃላፊነትና የፍልሰት ምርምርን ለማጠናከር እየተከናወኑ ያሉ ዋና ዋና ተግባራትን በዝርዝር አቅርበው ውይይት ተደርጓል፡፡

በፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም አያሌው በበኩላቸው “የፍልሰት ምርምር ሚና በኢትዮጵያ የፍልሰት አስተዳደር” በሚል የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን፤ የአገሪቱን ተጨባጭ የፍልሰት ሁኔታዎችን፣ የሕግና የአደረጃጀት ማዕቀፎችን፣ የምርምርን ሚና እንዲሁም በምርምር ሳይንሳዊ ማስረጃ ሊቀርብባቸው የሚገቡ የፍልሰት ዋና ዋና ጉዳዮችን ለይተው አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ የፍልሰት ምርምርን ለማጠናከር የተፈረመው የሶስትዮሽ የመግባቢያ ስምምነት በሁለቱ ዓለም አቀፍ ተቋማትና በኢትዮጵያ የተመረጡ ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የጋራ ምርምሮችን ለማድረግ፤ በፍልሰት ምርምር ዙሪያ የአቅም ግንባታን ለማጠናከር እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎች የሚካሄዱ የፍልሰት ምርምሮችን ለመደገፍ ያለመ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡

Tagged Under: capacity • Capacity Building • centre • Collaboration • german • higher education development • Human Rights Violations • Human Trafficking • initiative • integration • international • International Collaboration • Irregular migration • memorandum • Memorandum of Understanding • Migration • Migration Management • Migration Research • ministry of education • policy recommendations • Research • research grants • understanding
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች