የንግድ/የቢዝነስ እና የሰብዓዊ መብት ብሔራዊ የድርጊት መርሃ ግብር ለማዘጋጀት የሚያስችል የማስጀመሪያ እና የምክክር መድረክ በዛሬዉ እለት በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ተካሂዷል፡፡
መድረኩን በንግግር የከፈቱት በፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና የሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርሚያስ የማነብርሃን የልማትና የእድገት እንቅስቃሴዎች ሰብዓዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ አንዲመሩ ለማስቻልና ሊወሰዱ ስለሚገቡ የጥንቃቄ እርምጃዎች ለመምከር መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዉ ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት አመታት መንግሥት በወሰዳቸዉ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ማሻሻያ ስራዎች የኢንዱስትሪ ልማት እንዲጨምር፣ምርትና ምርታማነት እንዲያድግ፣ሀገር በቀል አልሚዎች በብዛትም ሆነ በማምረት አቅም እንዲያድጉ እና የዉጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር ማድረጉንም አያይዘዉ አዉስተዋል፡፡
በመሆኑም የእነዚህ ተቋማት ለአገሪቱ ዘላቂ ልማት እና እድገት የሚጫወቱት ሚና ምልኡ የሚሆነዉ የቢዝነስ እንቅስቃሴያቸዉ የሰዎችን መብት ባከበረ እና የመብት ጥሰትን ማስቀረት በሚያስችል ሁኔታ ሲመራ መሆኑንም ሚኒስትር ዲኤታዉ ተናግረዋል፡፡
በዚሁ መሠረትም የድርጊት መርሃ ግብሩን ለማዘጋጀት ጉዳዩ ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በመምከር የአብይ እና የባለሙያዎች ኮሚቴዎች ማዋቀር መቻሉንና ሌሎች ተያያዥ ተግባራት መከናወናቸዉን በመጠቆም ፍትሕ ሚኒስቴር በአዋጅ በተሰጠዉ ሥልጣን መሠረት የድርጊት መርሃ ግብሩን የማዘጋጀት ስራዉን እየመራ የማስተባበር ሚናዉን እንደሚወጣ በመግለፅ በዚሁ ተግባር ላይ የሚሳተፉ ተቋማት ለዓላማዉ መሳካት የበኩላቸዉን አበርክቶ በባለቤትነት ሰሜት እንዲወጡ አደራ በማለትና ድጋፍ ላደረጉ አካላት ምስጋና በማቅረብ የመጀመሪያዉ ዉይይት መድረክ በይፋ መከፈቱን አብስረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ክብርት ወ/ሮ ራኬብ መሰለ በበኩላቸዉ በሁሉም የንግድ ተቋማት ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ የማድረግ ኃላፊነት የመንግሥት መሆኑን በመጠቆም ተቋሙ በንግድ ድርጅቶች ላይ ባካሄዳቸዉ ክትትሎች በርካታ ክፍተቶች መኖራቸዉን ማረጋገጥ መቻሉንና እነዚህን ክፍተቶች ለመቅረፍና የመፍትሄ ርምጃዎችን ለማመቻቸት የንግድ እና የሰብዓዊ መብት ብሔራዊ የድርጊት መርሃ ግብር መዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን በመጠቆም ይህ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡
ቀጥሎም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቢዝነስና የሰብዓዊ መብት መርሆዎች እና ዓለም ዓቀፍ አዝማሚያዎችን አስመልክቶ የተዘጋጀ ጽሑፍ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቢዝነስና ሰብዓዊ መብቶች ባለሙያ በሆኑት በሆኑት ኦኖኑጁ አኮዋራጎማ (Mr ononuju okwaraogoma) ፣ የንግድና የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ በኢትዮጵያ የሚል ጽሑፍ ደግሞ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ዳይሬክተር ዶክተር ዶ/ር ብራይትማን ገብረ ሚካኤል አማካኝነት ቀርቧል፡፡
እንዲሁም ተቋማት የንግድና የሰብዓዊ መብት የብሔራዊ የድርጊት መርሃ ግብር በመንደፍ ሂደት ዉስጥ የሚኖራቸዉን ሚናና ሊከተላቸዉ የሚገቡ ሂደቶች የሚል ጽሑፍ በፍትሕ ሚኒስቴር የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር ዳይሬክተር በሆኑት በአቶ አወል ሱልጣን አማካኝነት ቀርቦ ዉይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በዉይይቱም በቀጣይ ለሚዘጋጀዉ የድርጊት መርሃ ግብር ግብአት የሚሆኑ ሀሳቦች የተሰባሰበ ሲሆን በቀጣይም የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል የንግድ/የቢዝነስ እና የሰብዓዊ መብት ብሔራዊ የድርጊት መርሃ ግብር ረቂቅ የማዘጋጀት ስራዉ የሚከናወን ይሆናል፡፡
በዚሁ መሠረትም የንግድና እና የሰብዓዊ መብት ብሔራዊ የድርጊት መርሃ ግብር በዛሬዉ እለት ማለትም ግንቦት 8 ቀን 2016 ዓ.ም በይፋ መከፈቱን በፍትሕ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽነ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ትህትና ጎአ አብስረዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ዶክተር ኤርሚያስ የማነብርሃን፣የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ክብርት ወ/ሮ አበባ እንዳለ፣የተከበሩ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ሃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግሰቴ፣የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ክብርት ወ/ሪት ራኬብ መሰለን ጨምሮ የመንግሥት ከፍተኛና መካከለኛ የስራ ሃላፊዎች ፣መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሀላፊዎችና ተወካዮች፣እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡