በፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ ሕግ ትምህርት እና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት በታክስ እና ጉምሩክና ወንጀሎች እና በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ምርመራ፤ ክስ እና የችሎት ክርክር የማስገንዘቢያ መጽሀፍት (Handbooks) የምርቃት ስነ-ስርዓት ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ በፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ኤርምያስ የማነብርሀን (ዶ/ር) መጽሀፍቱ የተዘጋጁት በተቋሙ በስራቸዉ ሰፊ ልምድ ባላቸዉ ባለሙያዎች ሲሆን ከዝግጅት በፊት የፍላጎት ዳሰሳ /need assessment/ ተደርጎ መሆኑን አውስተዋል፡፡ የመጽሀፍቱ ህትመት ለእዉቀት ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ ማሳያዎች ናቸዉ ያሉት ሚኒስትር ዲኤታዉ በማጣቀሻነት እንደሚያገለግሉና የሕግ ግንዛቤን ለማሳለጥ እንደሚጠቅሙም አክለው ገልጸዋል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ በበኩላቸዉ መሰል የግንዛቤ ማስጨበጫ መጽሀፍት ከዚህ ቀደም ያልተለመደ እንደነበር አዉስተዉ አሁን የተዘጋጁት እነዚህ መጽሀፍት ከስራዉ ጋር በቀጥታ የሚገናኙ መሆናቸዉን ገልጽዋል፡፡ አክለውም በቀጣይ የሚደረጉ ተመሳሳይ የህትመት ስራዎች በተሻለ ደረጃ/ standard/ እንዲዘጋጁ ትኩረት መስጠት ያሻል ብለዋል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸዉ ወርቁ በበኩላቸው ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ለአስፈጻሚዉ አካል ግንዛቤ ማስጨባጫ የሚሆኑ መጽሀፍት /Handbooks/ እየታተሙ እንደሆነ ገልጸዉ ህገወጥ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ መጠቀም/ Money laundry/፣ የሙስና ወንጀል እና ልዩ የስነ-ስርዓት ሕግ እና ሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር መጽህፍት /Handbooks/ ባለፉት አመታት ተዘጋጅተዉ የተሰራጩ ሲሆኑ በቀጣይም በዝግጅት ላይ ያሉ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡
አያይዘዉም በዝግጅቱ ላይ የተሳተፉትን ባለሞያዎች እና ህትመቱን ያገዘዉን የአዉሮፓ ህብረት አመስግነዉ ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስረክበዉ በወቅቱ ለተጠቃሚዎች የማድረስ ስራ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
በምርቃ ስነስርኣቱ ላይ የተሳተፉት ከልዩ ልዩ የስራ ክፍሎች የተወከሉ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች መጽህፍቱ ለዐቃቢያነ ህጎች በማጣቀሻነት እንደሚያገለግሉ በቀጣይም በሌሎች መስኮች ላይ ለማዘጋጀት በር እንደሚከፍትም ተናግረዋል፡፡