የንግድና የሰብዓዊ መብቶች ብሔራዊ የድርጊት መርሐ ግብር ለማዘጋጀት ያለመ የግብአት ማሰባሰቢያ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች መካሄዳቸው የቀጠለ ሲሆን በሃረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትም በተመሳሳይ ማካሄድ ተችሏል።
ኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሰብዓዊ መብቶች ዳሬክቶሬት ከተለያዩ አጋር አካላት እና የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጋር በመሆን ባዘጋጁት በዚህ መድረክ ላይ በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ የሐይማኖት አባቶች፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ሲቪል ማህበራት፣ ከልዩ ልዩ የንግድ ተቋማት፣ እንዲሁም የመንግስት ተቋማት የተወከሉ ባለድርሻ አካላት የተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በመድረኩ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ለታ በዳዳ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የሰብዓዊ መብቶች የድርጊት መርሐ-ግብርን በተለያዩ ጊያዜያት በማዘጋጀት ስትተገበር የቆየች መሆኑን ጠቅሰው በአሁን ሰዓት ደግሞ ለአገሪቱ አዲስ የሆነውን የንግድና ሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሃ-ግብር ለማዘጋጀት አገር አቀፍ ዳሰሳዊ ጥናት ከማካሄድ ጀምሮ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን በመጥቀስ የመድረኩ ተሳታፊዎች የተሟላ ግብዓት በመስጠት መንግሥት ለሰብዓዊ መብቶች መከበር እያደረገ የሚገኘውን ሂደት እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩም ንግድና ሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ የሚልና የሰብዓዊ መብት ጽንሰ ሐሳብ፤ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት መርሆችና መመሪያዎች፤ እንዲሁም ብሄራዊ የንግድና ሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሃ-ግብር ለማዘጋጀት የተከናወኑ ምልከታዎችና የተገኙ ግብረ መልሶችንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን የሚያብራራ ሰነድ በቴክኒክ ኮሚቴ አባላት በዝርዝር የቀረበ ሲሆን፣ ይህንንም ተከትሎ ተሳታፊዎች በተለያዩ የቡድን አደረጃጀቶች በመከፋፈል ለውይይት መነሻ እንዲሆኑ ተደርገው በተዘጋጁ ጥያቄዎች ላይ ውይይት በማድረግ ለግብዓት የሚሆኑ ነጥቦችን አንስተዋል።
ተመሳሳይ የግብዓት ማሰባሰቢያ የምክክር መድረኮች በተያዘላቸው ጊዜ መሰረት በተቀሩት ክልሎች እንደሚካሔድም ተጠቁሟል።