ህጎች ተረቀዉ ከመፅደቃቸዉና ስራ ላይ ከመዋላቸዉ በፊት ከህብረተሰቡና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት በበይነመረብ አስተያየት የሚሰበሰብበት ኢ-ኮንሰልቴሽን ፖርታል በፍትሕ ሚኒስቴር፣በኢኖቬሽን ሚኒስቴር እና በጀርመኑ ጂ.አይ.ዜድ በጋራ ተዘጋጅቶ በዛሬዉ እለት ከፌደራል ተቋማት ለተዉጣጡ የሕግ እንዲሁም የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ክፍል ባለሙያዎች ሥልጠና ተሰጥቷል።
በሥልጠናው ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ፣ በኢትዮጵያ የሕግ ማርቀቅ ሂደት ውስጥ ሁሉም አካላት የሚሳተፉበት አሰራሮችን መፍጠርና ተግባራዊ እያደረጉ መሄድ በየደረጃው ባሉ የመንግሥት አካላት የታመነበት መሆኑን ገልፀው ይህንኑ ተግባር የሚያግዙ ማንዋሎች ተዘጋጅተው ስራ ላይ መዋላቸውን አስታውሰዋል።
የሥልጠናው ተሳታፊዎች ወደየተቋማቸው ሲመለሱ በቀጣይ ስራዎችን በሚያከናዉኑበት ወቅትም በሕዝብ በተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀውን የሕግ አወጣጥና አረቃቀቅ ማንዋል እንዲሁም በፍትሕ ሚኒስቴር የወጡ መመሪያችን በሚገባ ተገንዝበው ስራቸውን ሊያከናውኑ እንደሚገባ ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በማሳሰብ፣ በዚህ ሂደት ውስጥ አንዱና መሠረታዊ የሆነው የማህበረሰቡን ሀሳብ ማሰባሰብ መሆኑን ተናግረዋል።
አያይዘውም ፍትሕ ሚኒስቴርን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት ሕግን እንደሚያመነጩና እነዚህ ህጎች ከመዉጣታቸዉ በፊት የህብረተሰቡን ተሳትፎ ማረጋገጥ እጅግ አስፈላጊ መሆኑንና ይህም ህጉ ሲወጣና ስራ ላይ ሲዉል ዉጤታማ እንደሚያደርገዉ እና የኦንላይን ሲስተሙ ከዚህ ቀደም ህጎች ከተረቀቁ በኋላ አስተያየትና ግብአቶችን ለመሰብሰብ በስብሰባ፣በጽሑፍና በመሰል መንገዶች ሲደረጉ ለነበሩ አሰራሮች አጋዥ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህ የኦንላይን ኢ-ኮንሰልቴሽን ፓርታል ማናቸውም ህጎች ከተረቀቁ በኋላ ለማህበረሰቡና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለአስተያየት ክፍት የሚደረግበት አገልግሎት በመሆኑ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባ ገልፀው ፓርታሉን በማዘጋጀት ሂደት ድጋፍ ላደረገው ጂ.አይ.ዜድ ምስጋና አቅርበዋል፤በቀጣይም ፓርታሉ በይፋ ለማህበረሰቡ የሚበሰር መሆኑን ጠቁመዋል።
የGIZ business environment and investment climate የቴክኒካል ድጋፍ ቡድን መሪ የሆኑት ሚስተር አልቤርቶ ጎሜዝ በበኩላቸዉ የኢ-ኮንሰልቴሽን ኦንላይን ፖርታል ለህብረተሰቡም ሆነ ለተቋማት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በመግለፅ እስካሁን ባለቸዉ ልምድ ኢትየጰያ የሕግ ጉዳዮችን ኦንላይን ላይ በመጫን አስተያየት የሚሰበሰብበት ሲሰትም በመዘርጋት አገልግሎት በመስጠት ያላት ቁርጠኝነት የሚበረታታ መሆኑን ጠቁመዉ፣ ድርጅታቸዉ እየተካሄዱ ባሉ የሕግና የሌሎች ዘርፎች የትራንስፎርሜሽን ስራዎች እገዛዉን ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ህጎች ሲረቀቁ አሳታፊ መሆን እንዳለባቸው የተለያዩ የሕግ ማእቀፎች በተለይም የአስተዳደር ስነ ሥርዓት ህጉ እንደሚያስገድድ ያስታወሱት ደግሞ በፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ጥናት ማርቀቅና ማጠቃለል ዳይሬክቶሬት ጀነራል ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ጉደታ ቀንአ ሲሆኑ ከተሳትፎ አንፃር ብዙ መሥራት እንደሚያስፈልግና በተለይም የኦንላይን ሲሰተሙ ተደራሽነትንና ተሳታፊነትን በማረጋገጥ ብሎም ዲጅታላይዜሽንን በማረጋገጥ የአገልግሎት ስርአቱ በቴክኖሎጂ የተደገፈ በማድረግ በኩል የሚኖረዉ ፋይዳ የጎላ መሆኑን ገልፀዋል።
ሲስተሙ FDRE E-consultation portal ማንዋል በተለያዩ የግብአት ማሰባሰቢያ መንገድ ሲሰበሰብ ከነበረዉ የሕዝብ ተሳትፎ በተጨማሪ በበይነመረብ አስተያየት የሚሰበሰብበት ሲስተም ሲሆን ህጎች ሲወጡ ከህብረተሰቡ በተጨማሪ የሚመለከታቸዉ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ሕግ እንዲሆን የሚያግዝ እና የፌዴራል ተቋማትንና ክልሎችን ያካተተ መሆኑን እንዲሁም ፓርታሉን በበላይነት የሚያስተዳድሩትና ፈቃድ ሰጭ አካል የሆኑት የፍትሕ ሚኒስቴር እና የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንደሆኑ ተገልፆል፡፡