በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ተስፋዬ ዳባ በተገኙበት የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ተገምግሟል፡፡
የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ተስፋዬ ዳባ እና የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ጉዳይ መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ጌቱ ታደሰ እንዲሁም የጽህፈት ቤቱ ዐቃብያነ ሕግ እና የድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች በተገኙበት የጽህፈት ቤቱ የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቃሲም አማን የጽህፈት ቤቱን የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን በሪፖርቱ በበጀት ዓመቱ በዕቅድ የተያዙ ዋና ዋና ግቦች አፈጻጸም፣ በዕቅድ አፈጻጸም ወቅት ያጋጠሙ ችግሮች፣ የተለዩ ጥንካሬዎች እና ውስንነቶች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በበኩላቸው የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ አጠቃላይ የዕቅድ አፈፃፀም እየተሻሻለ መምጣቱን እና በዚህም አበረታች ውጤት መመዝገቡን ጽህፈት ቤቱ ባለው ውስን የሰው ኃይል የተነሳ በብዙ የስራ ጫና ውስጥ ሆነው ይህ ውጤት እንዲመዘገብ በማስቻላቸው ምስጋናቸውን በማቅረብ ጽህፈት ቤቱ ካለበት ከፍተኛ ኃላፊነት አንፃር በጽህፈት ቤቱ የሚከናወኑ ስራዎች በፍትሕ ስርዓቱ ላይ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ በቀጣይም ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በአጠቃላይ በቀረበው ሪፖርትም በበጀት ዓመቱ በቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የዕቅድ አፈፃፀም ወቅት የታዩ ጥንካሬዎችን፣ ውስንነቶችን እና እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ዐቃብያነ ሕግ እና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች የተነሱ ሲሆን፣ ለተነሱት ጥያቄዎችንና አስተያየቶችንም ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ተገቢውን ማብራሪያና ምላሽ በመስጠት እና የቀጣይ የስራ አቅጣጫዎችን በማሰቀመጥ ግምገማው ተጠናቋል፡፡