በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ከወንጀል ጥቆማ ጀምሮ፣ የወንጀል ምርመራ፣ የዐቃቤ ሕግ ውሳኔ፣ ክርክር እና የፍርድን የወንጀል መረጃ እና የስራ ሂደት ማስተዳደር የሚያስችል የቴክኖሎጂ ስርአት በፍትሕ ሚኒስቴር፣ በፌዴራል ፖሊስ እና በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ በማልማት ሂደት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ኮሚቴ የፕሮጀክቱን ሂደት በመገምገም የስራ አቅጣጫና መመሪያ ሰጥቷል፡፡
የፍትሕ ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሐና አርአያስላሴ በአዲስ የተቀላቀሉትን የአስተባባሪ ኮሚቴ አባላት እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት እንደገለፁት ይህ ፕሮጀክት የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ስርአቱን ዲጂታላይዝ በማድረግ ውጤታማና ቀልጣፋ እንደሚያደርገው ብሎም አገራችን የያዘችውን የ2030 ዲጂታል ኢትዮጵያ ራዕይ በወንጀል ፍትሕ ዘርፍ እውን ለማድረግ እንደሚያግዝ ገልፀዋል፡፡
እንደዚህ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የወንጀል ፍትሕ ዘርፉ የጋራ መሰረተ ልማት (Digital Public Infrastructure) ሆነው እንደሚያገለግሉ ተጠቁሟል፡፡ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ኮሚቴ ከአማካሪ ድርጅቱ እና ከአልሚው የኢትዮጵያ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በቀረበው ገለፃና ማብራሪያ ላይ ውይይት አድርጓል፡፡
ቀድሞ በተደረገው የስራ ሂደት ፍላጎት ሰነድ (Business Requirement Document) ጥናት መሰረት የተዘጋጀውን እና በአማካሪ፣ በቴክኒክና በስራ ቡድን አባላት ተገምግሞ የቀረበውን የሶፍትዌር መስፈርቶች መግለጫ (Software Requirement Specification) ጥናት ሰነድ መሰረት በማድረግ ቀጣይ ስራዎች በተቻለ ፍጥነት እንዲከናወኑ እንዲሁም በቀጣይ ስርአቱን ለመተግበር የሚያስችል የሰው ኃይልና የባለሙያ እንዲሁም የመሰረተ ልማት ዝግጅት ስራዎች ከወዲሁ ተጠናክረው እንዲደረጉ በአስተባባሪ ኮሚቴው አቅጣጫና የስራ መመሪያ በመስጠት ውይይቱ ተጠናቋል፡፡