የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር ብሔራዊ የትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ከአለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅትና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር የዓለም አቀፉ የፍልሰት ስምምነትን(GCM) ተግባራዊ ለማድረግ ያለመ የግንዛቤ መፍጠሪያ የወይይት መድረክ የብሔራዊና ክልላዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡
በዚህ መድረክ ላይ የዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅ የኢትዮጵያ ቢሮ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቢባቱ ዋኔ በተወካያቻው አማካኝነት ባስተላለፉት መለዕክት እንደገለፁት የግንዛቤ ፈጠራ የውይይት መድረኩ ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የብሔራዊና ክልላዊ የትብብር ጥምረት ተወካዮች ስለሰነዱ ይዘት እንዲረዱ ለማድረግ፣ ልምድ ለመለዋወጥ እንዲሁም ለስምምነቱ የትግበራ እቅድ ዝግጅት የሚረዱ ግብዓቶችን ለማሰባሰብ የሚረዳ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
አክለውም ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የፍልሰት እንቅስቃሴ የሚደረግባት ሀገር በመሆኗ በቀጣይነት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ከግለሰብ እስከ ማኅበረሰብ ድረስ በየደረጃው የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን እየፈቱ ለመሄድ የስምምነቱ ተግባራዊ መደረግ ከፍተኛ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በመድረኩ ላይ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና የሰብዓዊ መብት መርሆች ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀውና ሀገራት ለተግባራዊነቱ በፈቃደኝነት መግባባት ላይ የደረሱበት ይህ ዓለም ዓቀፍ የፍልሰት ስምምነት(GCM) ተግባራዊ ለመሆን የሚያስችሉት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸው ተመለካቷል፡፡
በዚሁ መድረክ ላይ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታን ወክለው መድረኩን በይፋ የከፈቱት በፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ የትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አብረሃም አያሌው በበኩላቸው ዜጎች በሀገር ውስጥና ውጪ የሚያደርጉትን የፍልሰት እንቅስቃሴ ከመነሻ እስከ መዳረሻው ድረስ ሰላማዊ፣ ፍትሀዊ፣ ቀላልና መደበኛ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያስችሉ ህጎችን ከማውጣት በተጨማሪ ዓለም ዓቀፍ የፍልሰት ስምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ በመከናወን ላይ የሚገኙ ዝግጅቶችን ጠቅሰው፤ መንግሥት ህጋዊ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና መደበኛ የፍልሰት እንቅስቃሴ እንዲኖር ፍላጎት ስላለው ይህንን ዓለም ዓቀፍ ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ ከሀገሪቱ ፖሊሲ፣ ስትራቴጄና የልማት እቅዶች ጋር አጣጥሞ እንዲሄድ ለማድረግ በርካታ ስራዎችን በማከናወኑ ኢትዮጵያ ዓለም ዓቀፍ የፍልሰት ስምምነትን (GCM) እውን ከማድረግ አንፃር ግንባር ቀደም ሀገር መሆን መቻሏል አመልክተዋል፡፡
በፌደራል እና በተለያዩ ክልሎች ከሚገኙ የመንግሥት ተቋማት፣ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም በሌሎች ሀገራት ከሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተወከሉ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በተገኙበት ለሁለት ቀናት በሚካሄደው በዚህ የግዛቤ መፍጠሪያ የውይይት መድረክ ላይ ዓለም ዓቀፍ የፍልሰት ስምምነት (GCM) ያካተታቸው 23 ዋና ዋና ዓላማዎች፣ የስምምቱ 10 መሠረታዊ መርሆዎች እና ተያያዥ ጉዳዮች ተነስተው ምክክር የሚደረግባቸውና በዚህም በቀጣይ ስምምነቱን በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ግንዛቤ የሚያዝበትና ግብዓት የሚሰበሰብበት መሆኑ ታውቋል፡፡