ከፍልሰት ተመላሽ ዜጎችን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም የሚያስችል አገር ዓቀፍ የፖሊሲ ምክክር መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር መስከረም 29/2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡
ይህ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ አገራዊ የፖሊሲ ምክክር መድረክ ዋና ዓላማዉ ከተመላሾች መልሶ ማቋቋም ጋር በተያያዘ የአገራችንን የሕግና የአደረጃጀት ማዕቀፎችን በተመለከተ ለባለድርሻ አካላቱ ግንዛቤ ማስጨበጥ ሲሆን፣ የፍልሰት ተመላሾችን መልሶ ማቋቋም ላይ ከዚህ ቀደም የተሠሩ ሥራዎችን በመገምገ በቀጣይ ተግባር ተኮር አቅጣጫዎችንም አስቀምጧል፡፡
በመድረኩ የተጎጂዎች እና ተመላሽ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በፖሊሲ፤በሕግ እና ተቋማዊ ማዕቀፎች፤ በማኅበራዊና፤ ኢኮኖሚያዊ መስክ መልሶ ማቋቋም ላይ ያተኮረ ዉይይት የተደረገ ሲሆን፣ በዋና ዋና የስደት መንስኤዎች እና ተመላሾችን በዘላቂነት ማቋቋምን የተመለከተ ጥናታዊ ጽሑፍ ቀርቧል፡፡
የተመላሾች ቁጥር ማሻቀብ፤የተጠናከር አገራዊ የመረጃ አያያዝ ሥርዓት አለመኖር፤ የሀብት ዉስንነት፤አገራዊ እና ዓለም ዓቀፋዊ ትብብሮች በተፈለገዉ ደረጃ አለመሆን፤ ተለዋዋጭ ዓለም ዓቀፋዊ እና አገራዊ ሁኔታዎች፤የተመላሾች ከፍተኛ ድጋፍ ላይ ጥገኛ መሆን እና አለመርካት በአፈጻጸም ወቅት የታዩ ተግዳሮቶች እንደነበሩ የተገለጸ ሲሆን፤ እንደአገር የሚታየዉን የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት በመንግሥት የታየዉ ቁርጠኝነት፤ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ተግባራዊ መሆኑ፤ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች መቀረጻቸዉና የሲቪል ማህበራት እና ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች ተሳትፎ እንዲሁም እየታየ ያለዉ መደበኛ የዉጪ አገር ሥምሪት በበጀት ዓመቱ የታዩ መልካም አጋጣሚዎች እንደነበሩም ተወስቷል፡፡
ተመላሾችን በአግባቡ ተቀብሎ አስፈላጊዉን ድጋፍ ከማድረግ እና በዘላቂነት ከማቋቋም ጎን ለጎን ወንጀሎችን በመከላከል ፍልሰትን ሕጋዊና ደህንነቱ የተረጋገጠበት በማድረግ፤ የፍልሰተኞችን ሰብዓዊ መብቶች ማስጠበቅ እና የሀገርን ደህንነት በማረጋገጥ የፍልሰትን መልካም እድሎች ወደ ሀገራዊ ልማት ለመቀየር የሁሉም መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ አስፈላጊ እንሆነም ተጠቁሟል፡፡