ቀደም ሲል በሀገራችን ከተካሄዱ ምርጫዎች ትምህርት በመውሰድ ወደፊት የሚካሄዱ ምርጫዎች በመልካም ስነምግባር የሚመሩ ግልጽ፣ ነጻ፣ ፍትሃዊ ሰላማዊ፣ ህጋዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እንዲሁም በህዝብ ተቀባይነት ያላቸው እንዲሆኑ ለማስቻል በምርጫ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ እጩዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት እና ደጋፊዎች የሚመሩበት ዝርዝር የስነምግባር ህግ ማውጣት አስፈላጊ በመሆኑ፤
የኢትዮጵያ ሕዝብ ባሳለፈው የረጅም ጊዜ የመንግስት ስርዓት ሲታገልለት የኖረውን የሕዝብ ስልጣን አመንጪነት፣ ባለቤትነትና ተቆጣጣሪነት መብት አጠናክሮ መቀጠል በሀገራችን ሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሳይሸራረፉ ተግባራዊ መሆኑን ለሰለጠነ ሰላማዊ ትግልና ውድድር ያላቸውን ፋይዳ በመገንዘብና በመቀበል፤
የምርጫ ቦርድ የፍትሕ አካላት እና የመገናኛ ብዙሃን ከማናቸውም የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃነትና በገለልተኛነት ህዝብን ማገልገል እንዳለባቸው እንዲሁም የሀገር መከላከያ ሰራዊት በህገ መንግስቱ መሰረት ተግባሩን ከፖለቲካ ፓርቲዎች ወገናዊነት ነፃ በሆነ አኳኋን እንዲያከናውን የተደረገ መሆኑን በመገንዘብ፤
ሦስቱ የመንግስት አካላት የግልጽነት፣የታማኝነትና የተጠያቂነት ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለባቸው የተቀበሉና ተግባራዊነቱንም ለማክበር እና ለማስከበር ቃል የገቡ መሆናቸውን በማጤን የፖለቲካ ፓርቲዎች ለተፈፃሚነቱ መቆም እንዳለባቸው በመገንዘብ፤
በዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ መቻቻልን ማስፈን ተገቢ በመሆኑና በምርጫ ሂደት ነጻ የፖለቲካ ዘመቻ ማካሄድ እንዲሁም ግልጽ ህዝባዊ ውይይትን ማጎልበት አስፈላጊ በመሆኑ፤
የፖለቲካ ፓርቲዎች በተስማሙባቸው ጉዳዮች በጋራ እየሰሩና በልዩነታቸው ላይ ደግሞ በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ ትግል በማካሄድና በህግ መሰረት የተካሄዱ ምርጫዎች ትክክለኛ ሂደትና ውጤት የህዝብ ውሳኔ መሆኑን በፀጋ ተቀብለው በመጓዝ በሀገር ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት መወጣት ያለባቸው መሆኑን በመገንዘብና ወደስልጣን ለመምጣት በሚያካሂዱት ውድድር ከጥላቻና ካለመተማመን የፀዳ፤ ጤናማ ግንኙነት ፈጥረው የሚንቀሳቀሱበትን ሁኔታ ማመቻቸት አስፈላጊ በመሆኑ፤
የፖለቲካ ፓርቲዎች በቅንነት፣ በመቻቻል እና ሰጥቶ በመቀበል መርህ እየተመሩ በሀገራችን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እና ዴሞክራሲያዊ ባህል እንዲጎለብት የማይተካ ሚና እንዲጫወቱ ለማስቻል፤
የህዝብ ውሳኔን በመጻረር የመንግስት ስልጣን ላይ መቆየትም ሆነ ከህገ-መንግስታዊ ሥርዓት ውጪ የመንግስት ስልጣን ለመያዝ የሚደረጉ ማናቸውም የሀገር ውስጥም ሆኑ የውጪ እንቅስቃሴዎች ተቀባይነት የሌላቸው መሆናቸውን በአፅንኦት ማረጋገጥ አስፈላጊ በመሆኑ፤
የስነምግባር አዋጁ ለመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ለሰብአዊ መብት፣ ለዴሞክራሲ፣ ለህግ የበላይነት እና ለሕዝቦች ሁለንተናዊ እድገት ያለውን ልዩ አስተዋጽኦ በመገንዘብ ፤ ለተፈጻሚነቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ መቆም የሚያስችላቸው ሁኔታ ማመቻቸት በማስፈለጉ፤
ማንኛውም ለምርጫ አገልግሎት ሊውል የሚችል በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኝ ሀብት፣ ንብረትና የአካባቢ መስተዳድር አካላት አገልግሎቶች ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በህግ መሰረት በፍትሀዊነትና ያለአድልዎ የሚሰጥበትን አሰራር ማጠናከር በማስፈለጉ፤
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የመምረጥና የመመረጥ መብቱን ለማረጋገጥ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ምንም አይነት ተጽእኖ ወይም እንቅፋት እንዳይ ደረግበት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን በመገንዘብ፤
የፖለቲካ ፓርቲዎች በሥነ-ምግባር አዋጁ ላይ ተከታታይ ትምህርትና ስልጠና የመስጠት፣ ግንዛቤ የመፍጠር እና ሌላውም እንዲያስተምር የማበረታታት ከፍተኛ ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን በግልጽ መደንገግ በማስፈለጉ፤
የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚያቀርቧቸውን የምርጫ አስፈፃሚዎች እና አሠራራቸው ወይም የምርጫም ሆነ ሌሎች ተያያዥ ችግሮች በዚህ አዋጅ መሰረት በመመርመር ተጨባጭ ሆነው ከተገኙ የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል አሰራር መዘርጋት በማስፈለጉ፤
ይህንን አዋጅ ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችል አሠራር መዘርጋት እንዲሁም በየደረጃው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቶች ማቋቋምና ስልጣንና ተግባራቸውንም በግልጽ መደንገግ ከፍተኛ ሕዝባዊ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን በመገንዘብ፤
የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰፊ ጊዜ በመውሰድ ተወያይተው የተስማሙባቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያላቸውን መርሆዎች ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ የያዘ አዋጅ መደንገግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 55 ንዑስ አንቀጽ (1) እና ንዑስ አንቀጽ (2)(መ) መሰረት የሚከተለው ታውጇል።
•
•
•
•
•
•
•