የፍትሕ ሚኒስቴር ከሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች ጋር በመተባበረ ትኩረቱን በወንጀል ነገር ገብተዉ የተገኙ ወጣት ጥፋተኞች ፍትሕ አስተዳደር ዙሪያ ያደረገ ሥልጠና ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ሥልጠና እየሰጠ ነዉ፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ ሕግ፣ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እንዳልካቸዉ ወርቁ ፍትሕ ሚኒስቴር የራሱን ባለሙያዎች ጨምሮ የፍትሕ ዘርፍ የአስፈፃሚ አካላትን አቅም ማጎልበት ሥልጣንና ኃላፊነት እንደተሰጠዉ ጠቁመዉ ይህንኑ ሀላፊነቱን ለመወጣት እስካሁን ባለዉ ጊዜ በርካታ ሥልጠናዎችን መስጠቱን ገልፀዋል፡፡
ከእነዚህ የፍትሕ ዘርፍ የአስፈፃሚ ተቋማት አንዱ ፖሊስ መሆኑንና በዛሬዉ እለት የሚሰጠዉ ሥልጠናም የዚሁ ተግባር አንዱ አካል ነዉ ሲሉ በወንጀል ዉስጥ ገብተዉ የተገኙ እድሜያቸዉ ከ9 እስከ 15 ዓመት የሆኑ ወጣት ጥፋተኞች በሚያጋጥሙበት ጊዜ በስራ ሂደት ዉስጥ ክፍተቶች በመስተዋላቸዉ ምክንያት ይህንን ችግር መቅረፍ የሚያስችል ዓላማ ይዞ የተዘጋጀ ሥልጠና መሆኑን አያይዘዉ ተናግረዋል፡፡
አያይዘዉም ሥልጠናዉ ከአሰልጣኞችና በተቋሙ የተወሰነ ብቻ ሳይሆን በጋራ በመሆን ዉይይት ተካሂዶበትና የጋራ መግባባት ላይ ተደርሶ የወንጀል ስነ ሥርዓት ህጉ ላይ በተቀመጠዉ መሠረት ስራዎች እንዲሰሩ ለማድረግ መዘጋጀቱም ተናግረዋል፡፡
ሥልጠናዉ በመጀመሪያዉ ዙር በሁለት ቀን ቆይታዉ በወንጀል ነገር ገብተዉ የተገኙ የወጣቶች ፍትሕ አስተዳደር ከዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች አንፃር፣የወጣቶች የወንጀል አስተዳደር መርሆች፣የወጣቶች የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር በአገራችን ህጎችና በተግባር ያለዉ ሁኔታ የሚሉ ሰነዶች ቀርበዉ ሰፋ ያለ የቡድን ዉይይት የሚካሄድባቸዉ ይሆናል፡፡
ሥልጠናዉ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ለድሬድዋ ፖሊስ ኮሚሽን የተሰጠ ሲሆን በተመሳሳይ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላትም በሁለት ዙሮች ተከፍሎ የሚሰጥ ሲሆን በቀጣይም የሁለተኛ ዙር ሥልጠና ተካፋዮች የሚሰጥ ይሆናል፡፡