የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ በሰዎች ንግድ ወንጀል መከላከልና ቁጥጥር ረገድ ያስመዘገበችውን መሻሻል አደነቀ

The US Department of State Acknowledged Ethiopia’s Improvement Towards Prevention and Control of Trafficking in Persons

ኢትዮጵያ በሰው የመነገድ ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እያከናወነች የምትገኘው ጥረት እየተሻሻለ ስለመምጣቱ የአሜሪካ መንግሥት ማስታወቁን የፍትሕ ሚኒስትር ድኤታ አቶ አለምአንተ አግደዉ ገለጹ፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እ.ኤ.አ የ2023 የዓለም አገራትን በሰው የመነገድ ወንጀል የመከላከልና የመቆጣጠር ዓመታዊ ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡

በዚሁ ሪፖርት መሠረት ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ለዓመታት ከቆየችበት ዝቅተኛ የአፈጻጸም ደረጃ (Watch List) በመውጣት ወደ ሁለተኛ ደረጃ ተሸጋግራለች፡፡

እ.ኤ.አ ሰኔ 15 ቀን 2023 ዓ.ም. ይፋ በተደረገው በዚሁ ሪፖርት የኢትዮጵያ መንግሥት በሰው መነገድ ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየወሰደ የሚገኛቸው ርምጃዎችና እያደረገ ያለው ጥረት እየተጠናከረ መጥቷል፡፡

መንግሥት በወንጀል ምርመራና አጥፊዎችን ለሕግ ለማቅረብ እየወሰደ የሚገኘው ርምጃ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ መቀጠሉን የገለጸው ሪፖርቱ፤ አዋጅ ቁጥር 1178/12 በሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮም አገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በወንጀለኞች ላይ የተወሰዱትን ቅጣቶች የሚያሳይ ዝርዝር መረጃ ለማቅረብ መቻሏንም ሪፖርቱ አድንቋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የሕግ አስከባሪ አካላትን አቅም ለመገንባት፤ የተጎጂዎች ቅብብሎሽ ስርዓትን ለማሻሻል፤ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ዝርዝር መረጃ ተደራሽ ለማድረግ፤ ከአረብና ከባሕረ-ሰላጤው አገራት ለሚመለሱ ተጎጂ ዜጎች የድጋፍ አገልግሎት በማቅረብ እንዲሁም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ለተገነቡት አምስት የፍልሰተኞች ምላሽ መስጫ ማዕከላት የመሬትና የተለያዩ ድጋፎችን በማቅረብ ረገድ እያሳየች የሚገኘው መሻሻል ደረጃዋ ከፍ እንዲል አድርጓል፡፡

ያም ሆኖ ለድንበር ተሻጋሪ በሰው የመነገድ ድርጊትን ለመከላከል የተሰጠውን ትኩረት ያክል ለአገር ውስጥ በሰው የመነገድ ወንጀሎች ተገቢ ትኩረት አለመሰጠቱ፤ በመንግሥት የሚተዳደሩ የተጎጂዎች ማቆያና እንክብካቤ ማዕከላት አለመኖር፤ የውጭ አገር ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎችን የወንጀል ተጠያቂነት ሥርዓት አለመዘርጋት እንዲሁም የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያሳይ ብሔራዊ የመረጃ ቋት ሥርዓት አለመልማት የሚሉት ጉዳዮች አገሪቱ ዝቅተኛ አፈጻጸም ያሳየችባቸው ጉዳዮች መሆናቸውን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡ በዚሁ መነሻም በቀጣይ ኢትዮጵያ ልታተኩርባቸው የሚገቡ ናቸው ያላቸውን ጉዳዮች በዝርዝር አስቀምጧል፡፡

ብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ሰብሳቢ የሆነው የኢፌዴሪ የፍትሕ ሚኒስቴር በሕግ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት የአገሪቱን ዓመታዊ በሰው የመነገድ ሪፖርት ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየና በተሻለ መልኩ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን ከሚመለከታቸው አካላት በማሰባሰብ ለአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መላኩ ይታወሳል፡፡

በዚሁ አግባብ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ የአገሪቱን የአፈጻጸም ሪፖርት በመመልከትና በተጨባጭ እየተከናወኑ የሚገኙትን ሥራዎች በመገምገም እ.ኤ.አ የ2023 ሪፖርትን ይፋ በማድረግ ኢትዮጵያን ሁለተኛ እርከን ላይ እንድትቀመጥ አድርጓል፡፡

በየዓመቱ የሚወጣው ይኸው የአሜሪካ መንግሥት ሪፖርት ወንጀሎቹን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ አገሪቱ ከሌሎች አገራት ጋር ለሚኖራት ግንኙነት እና ለምታደርገው ድጋፍ መነሻ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡

በተያዘው የፈረንጆች ዓመት ኢትዮጵያ ያሳየችው መሻሻልም በሰው የመነገድ ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እያከናወነች የሚገኘውን ጥረት የበለጠ እንደሚያግዝና አቅም እንደሚፈጥር እንዲሁም በክፍተት የተለዩ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚጠቅም ሚኒስትር ድኤታዉ አቶ አለምአንተ አግደዉ ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትር ድኤታዉ አያያዝዉም በወንጀሎቹ ምክንያት በዜጎች ላይ እየደረሰ ካለው አስከፊ የሕይወት፣ የአካልና የደኅንነት ሥጋት አንጻር እየተደረጉ ያሉት ጥረቶች በቂ ባለመሆናቸው ሪፖርቱ የሚመለከታቸዉ ተቋማት በቅንጅት የበለጠ መሥራት እንደሚጠበቅባቸዉ የሚያስገነዝብ በመሆኑ በዚሁ አግባብ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ከሁሉም አካላትና ከጥምረት ጽ/ቤቱ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡

Tagged Under: (tip) 2023 amharic building capacity criminal justice reform department enforcement human Human Trafficking international organization for migration (iom) law legal framework list national action plan persons report state tier tier 2 trafficking trafficking in persons Transnational crime us department of state Victim protection watch list
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች