በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ የሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአራት ረቂቅ አዋጆች አስመልክቶ ከፍትሕ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች እና ከአስረጅዎች ጋር የካቲት 30/ 2015 ዓ.ም ተወያይቷል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው ውይይት ያደረገው፤ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና ከቱርክ ሪፐብሊክ መንግስታት ጋር ወንጀለኞችን አሳልፎ ለመስጠት እንዲሁም በወንጀል ጉዳዮች ላይ የጋራ የሕግ ትብብር ስምምነቶችን ለማፅደቅ በቀረቡ ረቂቅ አዋጆች ላይ ነው፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት፤ ከሁለቱ ሀገራት ጋር የሚደረጉ ስምምነቶች የሀገራቱን ሉዓላዊነት እና የባንክ ሚስጥሮችን የጠበቁ መሆናቸውን ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት አያይዘውም፤ አንድ በወንጀል የሚጠረጠር ግለሰብ ተይዞ ከወንጀሉ ነጻ ከሆነ ካሳ የሚከፈልበትን ሁኔታ በረቂቅ አዋጁ ማስቀመጥ እንደሚገባ አባላቱ ሃሳብ አንስተዋል፡፡
አባላቱ አክለውም፤ ረቂቅ አዋጁ ከወንጀል ሥነ-ስርአቱ ሕግ እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር እንዳይጣረስ በደንብ ማየትና መረዳት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ አቶ አለምአንተ አግደው በበኩላቸው፤ ረቂቅ አዋጁ ዓለም አቀፋዊ መርሆችን እና ተሞክሮዎችን ያካተተ መሆኑን ጠቁመው፤ ረቂቅ አዋጁ ጸድቆ በስምምነቱ መሠረት ወደ ሥራ ሲገባ ከአሁን በፊት በወንጀል የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን በሕግ ተጠያቂ ማድረግ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ጉዳዮች ዐለም አቀፍ ትብብር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ የሱፍ ጀማል በበኩላቸው፤ ከባንክ ሚስጥራዊነት ጋር በተያያዘ በሙስና ወንጀል ተጠርጥሮ የአንድን ሀገር ገንዘብ ወደ ሌላ ሀገር አሸሽቶ ከተገኘ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት የፍርድ ቤት ትእዛዝ በመቀበል ተፈጻሚ ማድረግ እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡
አቶ የሱፍ አክለውም፤ በወንጀል የሚጠረጠር ግለሰብ ወደሚፍለግበት ሀገር ሲሄድ የትራንስፖርት ወጪው የሚሸፈነው በትብብር ጠያቂው ሀገር እንደሆነ እና ሀገሪቱ ካላት የኢኮኖሚ አቅም አንጻር በወንጀል ለሚጠረጠረው ግለሰብ ካሣ የማትከፍል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም ረቂቅ አዋጁ የፖለቲካ ጥገኝነት የሚጠየቁ አካላትን እንደማያካትት የስራ ኃላፊዎቹ ጠቁመዋል።
ምንጭ:- የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት