የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር በሀገራችን የሚፈጸሙ የታክስና የጉሙርክ ወንጀሎችን ለመከላከል በትኩረት እየሰራ መሆኑን በተቋሙ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ወንድዬ ብርሀኑ ገለጹ፡፡
የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት የታክስ እና ጉምሩክ ህጎች ተገዥነትን ለማረጋገጥ በሚደረግ ሂደት ውስጥ የታክስ ወንጀሎችን በፈፀሙ ግለሰቦች ላይ ክስ በማቅረብ እና በማስቀጣት የታክስ ተገዥነትን ለማረጋገጥ የሚደረገውን እንቅስቃሴ የሚያግዝ የስራ ክፍል ነው ሲሉም ምክትል ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
ምክትል ዳይሬክተሩ አክለውም ፍትሕ ሚኒስቴር የታክስና የጉሙርክ ወንጀሎች በመከላከሉ ረገድ ኃላፊነቱን በሚፈለገው ልክ ለማከናወን ያግዘው ዘንድ ከጉምሩክ ኮሚሽን፣ ከገቢዎች ሚኒስቴር፣ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አንስተው ከሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮም ከተቋማቱ ጋር የታክስ እና የጉሙርክ ወንጀሎችን ለመከላከልና አጥፊዎችን በሕግ ተጠያቂ ማድረግ የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም በልዩ ሁኔታ በጋራ ለመሥራት ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል፡፡
የስምምነቱ ዋና ዓላማ የታክስና የጉሙርክ ሕግን ማክበር ኃላፊነት በሕግ የተጣለባቸው ተቋማት የታክስ ህጎችን በመተላለፍ የሚፈጸሙ የታክስ ወንጀሎችን በመከላከል የታክስ አስተዳደሩን የበለጠ ውጤታማ በማድረግ ኢኮኖሚ የሚያመነጨውን ገቢ በብቃት ለመሰብሰብ የሚያስችል ቅንጅታዊ አሠራር መዘርጋት በማስፈለጉ፣ ኮንትሮባንድና ሌሎች የንግድ ማጭበርበር ወንጀሎች በህጋዊ የንግድ እንቅስቃሴ፣ በሕዝብ ደኅንነት በመንግሥት ገቢ እና በሌሎች ማኅበራዊ እድገቶች ላይ የሚያስከትሉትን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመከላከል የተቀናጀ እና ጠንካራ ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ የስምምነቱ ዋና ዋና ዓላማዎች ናቸውም ሲሉ አክለዋል፡፡
በተጨማሪም ቀልጣፋና ውጤታማ የታክስና የጉሙርክ ሕግ ማስከበር እርምጃዎችን ለመውሰድ እና የታክስና የጉሙርክ ወንጀል ምርመራን፣ የክስ ሂደቱን ለሚመሩት ተቋማት መረጃ አደራጅቶ በፍጥነት ለማቅረብ እና አጥፊዎች ላይ ፈጣን ውሳኔ በመስጠት ታከስ የሚያጭበረብሩ፣ኮንትሮባንድና ሌሎች የንግድ ማጭበርበር የሚፈጽሙ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ የተቀናጀ ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ የአገራችንን ኢኮኖሚ ደኅንነት ማረጋገጥ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የስምምነት ፊርማውን ከተቋማቱ ጋር በመፈራረም ወደ ስራ ገብተናል ብለዋል፡፡
በዚሁ መሠረት ፍትሕ ሚኒስቴር የታክስ እና ጉምሩክ ወንጀሎችን ከመከላከል አንጻር በክልሎች አካባቢ ይታይ የነበረውን ክፍተት ለመቅረፍ በአዳማ፣ ባህርዳር፣ በኮምቦልቻ ፣በጎንደር እና በጅግጅጋ አካባቢ የሚፈፀሙ የታክስ እና ጉምሩክ ወንጀሎችን በተመለከተ 5 ቅርንጫፎችን በመክፈትና ዐቃቢያነ ህጎችን በመመደብ ወደ ስራ መግባቱን አንስተዋል፡፡ በዚህ ሂደትም የጉምሩክ ኮሚሽን እና ገቢዎች ሚኒስቴር አሰፈላጊውን ቢሮ እና አስፈላጊ የቁሳቁስ ድጋፎችን በማቅረብ ተገቢውን እገዛ እያደረጉ ወንጀሉን በመከላከሉ ረገድ በቅንጅት እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡
የኢኮኖሚ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት በበጀት ዓመቱ በዕቅድ ከያዛቸው ተግባራት መካከል በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በታክስና ጉሙርክ ወንጀሎች ዙሪያ 1056 መዛግብት ላይ በፍርድ ቤት ክርክር ተደርጎ በ169 መዛግብት 207 ተከሳሾች ጥፋተኛ ተብለው ቅጣት ተላልፎባቸዋል ሲሉ ምክትል ዳይሬክተሩ የገለጹ ሲሆን ሌሎች ቀሪ ስራዎችንም በማከናወን ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ የታክስ እና ጉምሩክ ወንጀሎች በሕዝብ፣ በመንግሥት እና በህጋዊ የንግድ ስርዓት ላይ የሚፈፀም ወንጀል መሆኑ ታውቆ ሁሉም ዜጋ ለታክስ ስርዓት ተገዥ እንዲሆን፣ይህን ተላልፎ የታክስና ጉምሩክ ወንጀል ላይ የተሰማሩ አካላት ካሉ ተገቢውን ጥቆማ በማቅረብ የታክስ ሕግ ተገዥነት እንዲረጋገጥ የበኩላችንን ኃላፊነት ልንወጣ ይገባል ሲሉም አቶ ወንድየ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡