የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የተጠሪ ተቋማትን 2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ገመገመ

The Federal Democratic Republic of Ethiopia Ministry of Justice Reviews the First Quarter Performance of the 2017 Budget Year Plans of its Affiliate Institutions

የፍትሕ ሚኒስቴር የተጠሪ ተቋማትን 2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና የተጠሪ ተቋማት አመራሮች በተገኙበት በትላንትናው እለት በአዲስ አበባ ገምግሟል፡፡ በግምገማው የአራቱም ተጠሪ ተቋማት የሩብ ዓመት ሪፖርታቸውን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

የግብር ይግባኝ ቅሬታዎችን በተመለከተ በአጠቃላይ 479 የይግባኝ መዛግብት የቀረቡ ሲሆን ለውሳኔ ከተቀጠሩት ውስጥ 187 መዛግብት ውሳኔ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ውሳኔ ካገኙት መካከል 105 የጉሙሩክ ሲሆን 82 መዛግብት ደግሞ የገቢዎች ሲሆኑ አፈጻጸሙ 97.4% መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በሰነድ ማረጋገጥና መመዝገብ ተግባር የማህበራት የመመስረቻና መተዳደሪያ ደንቦችን፣ የውል ስምምነት፣ውክልና፣ ኑዛዜ የማረጋገጫና የመሻሪያ፣ የፊርማ ናሙና፣ የጥብቅና ፈቃድ እና የእግድ እና የተለያየ ይዘት ያላቸው ከሕግና ከሞራል በማይቃረኑ መልኩ የተረጋገጡ ሰነዶችን በፌዴራል ደረጃ በአምስቱ የአገልግሎት ዘርፎች 238,608 ጉዳዮችን ለማስተናገድ በዕቅድ ተይዞ 221,190 ጉዳዮች በማስተናገድ 93% ማከናወን የተቻለ ሲሆን፤

የተለያዩ የማህበራት ሰነዶች የመመስረቻ ጽሁፍና የማሻሻያ ቃለጉባዔ ሰነዶችን መርምሮ ማረጋገጥና መመዝገብን በተመለከተ ብዛታቸው 10,802 ዕቅድ ተይዞ ብዛታቸው 11,250 የሆኑትን ማረጋገጥና መመዝገብ በመቻሉ አፈጻጸሙ 104% ሆኗል፡፡

በሌላ በኩል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ክትትል ግምገማ እና ምርመራ በተመለከተ 174 አዲስ ድርጅቶችን ለመመዝገብ ታቅዶ 152 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ማለትም 149 አገር በቀል እና 3 የውጭ ድርጅቶች ተመዝግቧል። ለሶሰት ተከታታይ ዓመት ሪፖርት ሳያስገቡና ህልውናቸውን ያላረጋገጡ 205 ድርጅቶች የነበሩ ቢሆንም 4ቱ ፋይላቸው ተጣርቶ ህልውናቸውን ያረጋገጡ ሲሆን 201 ድርጅቶች ተዘግቶ ባንካቸው የማገድ ፤ ፋይላቸውም በማጣራት ለፈንድ አስተዳደር እና ንብረት ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ የማስተላለፍ እና 32 ሰነዶችን በማጣራት የማረጋገጥ ስራ ተሰርቷል፡፡ ህልውና ማረጋገጥ ጎን ለጎን ፋይላቸው ከሚመለከታቸው ስራ ክፍሎች ወደ ስራ ክፍሉ በወቅቱ ሳይቀርቡ ነግር ግን ሪፖርት ማቅረብ ሲገባቸው ባለማቅረባቸው ጋዜጣ ላይ ያልወጡትን 68 ድርጅቶች ሪፖርት ያላስገቡበትን ምክንያት እንዲያስረዱ በደብዳቤ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡ የሪፖርት ግምገማን በተመለከተም የ264 ድርጅቶች ኦዲት ሪፖርት ተገምግሟል፡፡

የታራሚዎችን የማረምና የማነጽ አገልገሎት አሰጣጥን ከማሳደግ አኳየያ በአጠቃላይ የእስረኞችን መረጃ በተመለከተ የፌዴራል ማረሚያ ቤት ወንድ 10,407 ሴት 690 ድምር 11,097 እና የክልል ማረሚያ ቤቶች የእስረኞች መረጃ ወንድ 83,331 ሴት 3,189 ድምር 86,520 በሀገር አቀፍ ደረጃ የእስረኞች መረጃ ወንድ 93,738 ሴት 3,879 ድምር 97,617 መሆኑን የተገለፀ ሲሆን ፤

የመሠረታዊ ፍላጎቶች አቅርቦት አገልግሎት አሰጣጥን መጨመር ጋር በተያያዘ በቀጠሮ እና በፍርድ 1,300 ወንድ 63 ሴት በድምሩ 1,363 አዲስ ገቢ የቀጠሮ እስረኞችን በፍ/ቤት ትእዛዝ መሠረት የተላኩ መሆኑን በማረጋገጥ ቅበላ ተደርጎ በማረሚያ ቤት ቆይታቸው መብትና ግዴታቸውን እንዲያውቁ በማድረግ በየካታጎሪያቸው ተደልድለው የፍትሕ ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ተደርጓል፡፡

የታራሚዎችን የትምህርትና ሥልጠና አገልግሎት ከማሳደግ አንጻር እንዲሁ የመደበኛ ቀለም ትምህርት 1,272 ታራሚዎች ምዝገባ ተከናውኖ የልየታ ስራ በመከናወን ላይ ሲሆን፤ በተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች መሰረተ ትምህርት 106 ታራሚዎች ምዝገባ እና ምልመላ በመከናወን ላይ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

የተለያዩ የገቢ አማራጮችን በመፍጠር ገቢን መሰብሰብን አስመልክቶ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን ከምዝገባና ከሌሎች አገልግሎቶች ብር 631,975.00፣ ማረሚያ ቤት ከሰብል ምርት፣ ከእንሰሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች፣ከመኖ ምርት፣ ከተለያዩ የአነስተኛ እደ ጥበብ ኢንዱስትሪ ምርቶች ሽያጭ 4,929,863.83 እና ከሰነዶች ማረጋገጥ እና ምዝገባ የተለያዩ አገልግሎቶች የተሰበሰበው ገቢ ብር 651,000,000.00 እንደሆነ በቀረበው ሪፖርት ላይ ተመላክቷል፡፡

ከዝርዝር ሪፖርቱ በተጨማሪ ተጠሪ ተቋማቱ በስራ ሂደት ያጋጠሟቸውን ችግሮች፣ የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎችን እንዲሁም ከፍትሕ ሚኒስቴር በኩል የሚፈልጉትን ድጋፍ እና ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል፡፡

በመቀጠልም የፍትሕ ሚኒስቴር አመራሮች በተጠሪ ተቋማቱ የቀረቡ ሪፖርቶችን መነሻ በማድረግ ጥያቄና አስተያየት አንስተዋል ፤እንዲሁም የየተቋሙ የስራ ኃላፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በመጨረሻም የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በቀጣይ ሁሉም ተቋማት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሯቸው የሚገቡ አቀጣጨዎችን እንደሚከተለው አስቀምጠዋል፡-

1. የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ዲጂታላይዜሽን – የተጀመሩ እና በሂደት ላይ ያሉ ስራዎች ትኩረት ሰጥቶ መጨረስ እና አዲስ መሰራት ያለበቸውን ትኩረት ሰጥቶ ለውጤት ማብቃትና አመራሩ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት አለበት፤

2.የሰነ-ምግባርና አገልግሎት አሰጣጥ – በስነ-ምግባር ዙሪያ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንዲሁም አገልግሎት አሰጣጣችንን ማሻሻል ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል ። በተጨማሪም በሚቀጥለው ሳምንት በሚጀመረው የጸረ ሙስና ንቅናቄ ላይ ትኩረት ስጥቶ መሥራት ያስፈልጋል።

3. ብሔራዊ መታወቂያ፡- በዚህ ዙሪያ ሰራተኞቻችን እና ዜጎች መታወቂያ እንዲመዘገቡና እንዲወስዱ ከሚመለከተው አስተባባሪ አካላል ጋር በመቀናጀት ትኩረት ስጥቶ መሥራት ያስፈልጋል።

4. በፈጠራ የታገዘ (ለየት ባሉ ኢንሺየቲቭ)መሥራት፡- ጉልህ ሆኖ ሊታይ የሚችል ስራ እንዲሁም አዲስ ነገር እንዴት ነው ልናመጣ የምንችለው የሚለውን ትኩረት ስጥቶ መሥራት ያስፈልጋል ሲሉ በሰጡት ቀጣይ የስራ አቅጣጫ ላይ አመላክተዋል፡፡

በግምገማው የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ኤርሚያስ የማነብርሀን (ዶ/ር) ፣የተጠሪ ተቋማት ክትትልና ድጋፍ አስተባባሪ ሆነው የተሰየሙትን የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት ክቡር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ እና የስትራቴጂክ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ መንግስቴ ተሳትፈዋል፡፡

Tagged Under: Budget Performance Public Administration
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች