የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አለምአንተ አግደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ ኒል ጄ ዋልሽ ጋር ፍሬያማ ውይይት አካሂደዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ተወካዩንና የልዑካን ቡድኑን ተቀብለው የተወያዩት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ቢሮው እስካሁን ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሕግ ጉዳዮች ዓለቀፍ ትብብር፣ ወንጀል መከላከል፣ ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ስትራቴጂን በማዘጋጀት ሂደት፣ በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመልስና ማስተዳደርዘርፍ፣ በሰው የመነገድ እና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን በመከላከልና በመቆጣጠር ዘርፍ፣ የወንጀል ጠቋሚዎች እና ምስክሮች ጥበቃ ረቂቅ የሕግ ማዕቀፍን በማዘጋጀት ሂደት እና በሌሎችም ተቋሙ ተልዕኮ ወስዶ በሚሰራባቸው ዘርፎች ላደረገው ከፍተኛ ድጋፍ የላቀ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የፍትሕ ሥርዓቱን ማጠናከር ለሰላም፣ ለእድገት እና ድህነት ቅነሳ የማይተካ ሚና ያለው መሆኑን አውስተው የፍትሕ ሥርዓቱን የማጎልበት ስራውን ከሚመለከታቸው ባለደርሻ አካላት በመተባበር አጠናክሮ መቀጠል አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም ቢሮው በሕግ ጉዳይ ዓለም አቀፍ ትብብር ዓለማቀፍ ትብብር፣ በወንጀል መከላከል፣ በነፃ የሕግ ድጋፍ፣ በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመልስና ማስተዳደር፣በወንጀል ጠቋሚዎች እና ምስክሮች ጥበቃ እና በሌሎችም ዘርፎች ተቋሙ እያከናወናቸው ላሉ ተግባራት ተከታታይና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
ሚ/ር ኒል ጄ. ዋልሽ በበኩላቸው ቢሮው በኢትዮጵያ ትርጉም ባለዉና ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲንቀሳቀስና ለፍትሕ ሥርዓቱ ከፍተኛ ድጋፍ እንዲያደርግ የፍትሕ ሚኒስቴር ከፍተኛ እገዛ እንዳደረገላቸው ገልፀው እና የለፍትሕ ሚኒስቴር አመራር ምስጋናቸዉን አቅርበው ግንኙነቱም ዓለማቀፍ ደረጃዉን የጠበቀ ግንኙነት ነው ሲሉ ገልፀዉታል።
ቀጥለዉም ቢሮው በተጠቀሱት ዘርፎች ማለትም በወንጀል መከላከል፣ ዓለማቀፍ ትብብር፣ ነፃ የሕግ ድጋፍ፣ በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመልስና ማስተዳደርየወንጀል ጠቋሚዎች እና የምስክሮች ጥበቃና ሌሎች ጉዳዮች ላይ በቀጣይ እና በዘላቂነት ለመደገፍ ፍላጎትና ዝግጁነት ያለው መሆኑን ገልፀዋል።
በመጨረሻም ሁለቱም ወገኖች በውይይቱ በተነሱት ጉዳዮች ላይ በጋራ እና በቅንጅት መሥራት በኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት ላይ አወንታዊ ለውጥ የሚያመጣ በመሆኑ ይህንኑ ለመፈፀም የጋራ አቋማቸዉን አንፀባርቀዋል።