የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ለሚዋዋሏቸው ዓለም ዓቀፍ ውሎች ተግባራዊ የሚሆኑ ናሙና ውሎች ከአሁናዊ ለውጦች ጋር በማጣጣም እንዲሻሻሉ ማድረጉን በተቋሙ የፍትሃ ብሄርና ፍትሕ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሄኖክ ተስፋዬ ገልፀዋል፡፡
ፍትሕ ሚኒስቴር በአዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6(4) ስር ተዘርዝረው ከተሰጡት የፍትሐ ብሄር ሥልጣን እና ኃላፊነት መካከል የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የሚዋዋሏቸውን ውሎች በመመርመር የሕዝብና የመንግሥትን ጥቅም የሚያስጠብቁ መሆናቸውን ማረጋገጥ አንዱና ዋነኛው ሲሆን ይህንኑ ኃላፊነት በተሻለ መንገድ መወጣት እንዲቻል ተቋማት የሚገለገሉባቸውን ውሎች ናሙና በዩ ኤስ ኤይድ ፍትሕ ፕሮጀክት ድጋፍ ከአለም አቀፉ የሕግ ኢንስቲቲዩት እና በሀገር ውስጥ ከሚገኙ በዘርፉ ልምድ ካላቸው የሕግ ባለሞያዎች ጋር በጋራ በመሆን የዳሰሳ ጥናት መከናወኑን አቶ ሄኖክ ተናግረዋል።
አያይዘዉም የፌዴራል መንግሥት ባለበጀት መስሪያ ቤቶች የሚዋዋሏቸው ውሎች የሕዝብና የመንግሥትን ጥቅም በተሻለ ማስከበር እንዲችሉ ታስቦ አስቀድመው በስራ ላይ በነበሩ ናሙና ውሎች፣ የተፈረሙ እና የተፈጸሙ ውሎች እንዲሁም በመንግሥት ተቋማት የውል አስተዳደር ዙሪያ የዳሰሳ ጥናት በማድረግ በግኝቱ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ከተደረገበት በኋላ የቀደሙትን ናሙና ውሎች በማሻሻል ሶስት የዓለም አቀፍ ውሎች ናሙና እንዲዘጋጁ መደረጉን ገልፀዋል፡፡
እነዚህ ማሻሻያ የተደረገባቸዉ ናሙና ዉሎችም የዓለም ዓቀፍ የዕቃዎች ግዢ፣ የአገልግሎት እና የግንባታ ዘርፍ ስራ ግዥ ዉሎች ማሻሻያ ናቸው።
በጥናቱ ውጤት እና በተዘጋጁት ናሙና ውሎች ዙሪያ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት በማድረግ በግኝቶቹ ዙሪያ መግባባት መደረሱ የተገለፀ ሲሆን ተሻሽለው የተዘጋጁትን ናሙና ውሎች ከዚህ ቀደም በመንግሥት መስሪያ ቤቶች ጥቅም ላይ ሲውሉ የነበሩትን ተክተው በስራ ላይ እንዲውሉ ለማስቻልም ለፌዴራል መንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን የተላኩ ሲሆን ባለስልጣኑ ተገቢውን ምርመራ ካደረገባቸው በኋላ ወደተግባር እንዲገቡ ለሁሉም ተቋማት እንደሚያሰራጭ ተገልጧል።
በቀጣይም ማሻሻያ ባልተዘጋጀላቸው የሌሎች የግዥ ዘርፍ ናሙና ውሎች ላይ የሚደረገው የዳሰሳ ጥናት እንደሚቀጥልና በቅርቡ ለሁሉም ውል ለሚያስፈልጋቸው የግዥ ዘርፎች የናሙና ውል ማሻሻያዎች በማድረግ ለባለስልጣኑ እንደሚቀርብ የገለፁት ዳይሬክተር ጀነራሉ የመንግሥት መስሪያ ቤቶችም በባለስልጣኑ በሚሰጠው አቅጣጫ እንዲሁም በሚላክላቸው ናሙና ውል መሠረት ስራቸዉን በመፈጸም የሕዝብና የመንግሥትን ጥቅም የበለጠ ማስከበር እንዲችሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴር ከተለያዩ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ጋር በጋራ በመሆን የግዙፍ የመንግሥት ፕሮጀክቶች ውሎች ላይ ድርድር በማድረግ፣ በተቋማት የተዘጋጁ ረቂቅ ውሎችን በመመርመር እንዲሁም ውሎችን በማርቀቅ ለተቋማት እያደረገ ያለውን እገዛ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የተገለፀ ተቋማትም በተለይም የፍትሐ ብሄር ጉዳዮቻቸውን ለፍትሕ ሚኒስቴር በማቅረብ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያገኙ እና የሕዝብና የመንግሥት ጥቅም በተሻለ እንዲከበር እንዲያደርጉ ዳይሬክተር ጀነራሉ መልእክታቸዉን አስተላልፈዋል፡፡