ሔኖክ ተስፋዬ ተፈራ

ዳይሬክተር ጄነራል
ጥቅምት 1፣ 2002 ዓ.ም. – አሁን

አቶ ሔኖክ ተስፋዬ ተፈራ በኢትዮጵያ በፍትሐብሔር ጉዳዮች መልካም ሥምን ያተረፉ ከ15 ዓመት በላይ ልምድ ያላቸው ዐቃቤ ሕግ ናቸው፡፡ አቶ ሔኖክ ከባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት በማዕረግ የሕግ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የተቀበሉ ሲሆን ከአምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ በሕግ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሶሻል ዎርክ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡ በተለያዩ ስመጥር ዓለምዓቀፍ ተቋማት ከሥራቸው ጋር በቀጥታ የሚገናኙ የተለያዩ ትምሕርትና ሥልጠናዎችንም ተከታትለዋል፡፡   

አቶ ሔኖክ ከጳጉሜ 2012 ዓ.ም ጀምሮ በፍትሕ ሚኒስቴር በፍትሐብሔር ፍትሕ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ጄኔራል ዳይሬክተር ጄኔራልነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በሥራ ዘመናቸው ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ የወንጀል እና የፍትሐብሔር ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግነት አንስተው በግልግል ዳኝነት እና ዓለምዓቀፍ ጉዳዮች አስተባባሪነት እንዲሁም በምክትል ዳይሬክተርነት በሥራ ክፍሉ ሲሳተፉ ቆይተዋል፡፡ አቶ ሔኖክ በስራቸው ላይ ለሚያሳዩት ታታሪነት፣ የላቀ ብቃት እና የሙያ ሥነ-ምግባር በብዙዎች የሚመሰከርላቸው ዐቃቤ ሕግ ሲሆኑ በኃላፊነት በቆዩባቸው ጊዜያትም ያላቸውን የአመራር ብቃት እንዲሁም ችሎታ መሰረት ያደረገ እውቅና በተከታታይ ለግላቸው እና ለሚመሩት የሥራ ክፍል በፍትሕ ሚኒስቴር የተሰጣቸው አመራር ናቸው፡፡ 

አቶ ሔኖክ ላለፉት 15 ዓመታት ከፍተኛ ሀገራዊ ፋይዳ ባላቸው የፌዴራል መንግሥቱ እና የተቋማቱ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የፍትሐ ብሔር፣ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ጉዳዮች ላይ የሕግ ምክርን በመስጠት፣ ድርድር በማድረግ እንዲሁም የውል ሰነዶችን በማዘጋጀት እና በመገምገም ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡ አገራችን በገባችባቸው የሁለትዮሽና ባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮች የሕግ ሰነዶችን እንዲሁም የሕግ ምክርን በማቅረብ ይታወቃሉ፡፡ ከዚህም አልፈው በአገር ውስጥ እና በዓለም ዓቀፍ መድረኮች ኢትዮጵያን እና መንግሥትን በመወከል በክርክር እና በድርድር በመሳተፍ ሕዝብና መንግሥት ሊያጡ የሚችሉትን ጥቅሞች ያስመለሱና ሊገኙ የሚችሉ ጥቅሞችን ያስጠበቁ ናቸው፡፡ አቶ ሔኖክ ያላቸውን የጥናት፣ የሕግ ትንተና፣ የክርክር እና የፖሊሲ መቅረፅ ችሎታ በሁሉም ደረጃ እና ሁኔታ ለሀገራቸው የሕግ ሥርዓት በተለይም ለፍትሐብሔር ፍትሕ አስተዳደር መሻሻል አውለዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ አገራዊ ጠቀሜታ ባላቸው በርካታ ጉዳዮች ላይ የግልግል ዳኛ እና አስታራቂ ሆነው ያገለገሉ እና በተለያዩ ዓለም ዓቀፍ የግልግል ዳኝነት እና የዳኝነት ተቋማት ኢትዮጵያን እንዲሁም የመንግስት ተቋማትን በቀረቡባቸው የኢንቨስትመንት፣ የንግድ እና ሌሎች ፍትሐብሔራዊ ክሶች ላይ በመወከል ከፍተኛ አስተዋጾ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ አቶ ሔኖክ ለተከታታይ ዓመታት ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ለሌሎች የዓለም ዓቀፍ የስምምነት ኮሚቴዎች የሚቀርቡ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ሪፖርቶችን በማዘጋጀት እና በማቅረብ ሂደት ውስጥ ትልቅ ሚና ያላቸው የቡድን አባል በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ። አቶ ሔኖክ በኢትዮጵያ የተለያዩ ሕጎች እና አሰራር ሥርዓቶች እድገት ውስጥ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል። የፌደራል መንግስት ተቋማት የዐቃቤ ሕግ የተቋማት ክትትል ሥራን ተከትሎ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያስችል የአሰራር ሥርዓትም ነድፈዋል። ከዚህ በተጨማሪ ልምዳቸውንና እውቀታቸውን ለሌሎች ዐቃቤያነ ሕግ በማካፈል ከእርሳቸው የሚማሩ ባለሙያዎችን ለማፍራት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ የሚገኙ ሲሆን ተገቢውን አመራር በመስጠት ለተቋሙ የተሰጠውን የሕዝብ እና የፌዴራል መንግሥቱን መብትና ጥቅም የማስከበር ተግባርና ተልዕኮ በሚዛናዊነትና በተገቢው የትኩረት ደረጃ በመስራት ግንባር ቀደም ሚና የተጫዎቱ ሲሆን አሁንም የድርሻቸውን ለማስቀጠል ዝግጁ ናቸው፡፡

የትምህርት ዳራ

  • ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ (በህግ የመጀመሪያ ዲግሪ)፣
  • አምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ (በህግ ሁለተኛ ዲግሪ)
  • አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (ሁለተኛ ዲግሪ በሶሻል ዎርክ)

ዜና