የፍትህ ሚኒስቴር አመራሮች "ዓድዋን እንዘክራለን፤ ኢትዮጵያን አፅንተን ለትውልድ እናሻግራለን!!" በሚል በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ውይይት አደረጉ

Ministry of Justice Leadership Holds Discussion on "Remembering Adwa, Strengthening Ethiopia for Future Generations"

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች በተገኙበት 129ኛው የአድዋ ድል በዓል “አድዋን እንዘክራለን ኢትዮጵያ አጽንተን ለትውልድ እናሻግራለን“ በሚል ለውይይት መነሻነት በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡

ዘንድሮ በኢትዮጵያ ለ129ኛ ጊዜ “አድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል!“ በሚል መሪ ቃል የተከበረውን የአድዋ የድል በዓል መነሻ በማድረግ የፍትሕ ሚኒስቴር ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች በተገኙበት መድረክ ለውይይት መነሻ የሆነውን ሰነድ በማቅረብ ገለፃ ያደረጉት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፈ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶክተር ኤርሚያስ የማነብርሀን ሲሆኑ በዚህም አድዋ የአባቶቻችን ምክር፣ የአመራርነት ብልሀት እንዲሁም አስደናቂ ጀግንነታቸው በሰፊው የታየበትን የነጻነት ትግል ሂደትና በትግሉ የተገኘው የአድዋ ድል በጥቁር ህዝቦች ዘንድ የፈጠረውን ኩራትና የአሸናፊነት መንፈስ በማንሳት አብራርተዋል፡፡

በውይይት መድረኩ በአድዋ ጦርነት ወቅት የአንገዛም ባይነት የነጻነት ትግሉ ላይ ከነበሩት ወንዶች ጋር እኩል ተሰልፈው ሚናቸውን በመወጣት ለድሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስላበረከቱ ሴቶች ትግል አስታውሰው በወቅቱ ንጉሰ ነገስቱ ጠርተውት ከነበረውና የወረኢሉ ቀጠሮ እየተባለ ከሚታወቀው የክተት ጥሪ ጀምሮ ከአምባላጌ እስከ አድዋ ድረስ የነበረውን አጠቃላይ ቅድመ ዝግጅትና የጦርነት ሂደት ወደ ኋላ ተመልሰው ሁነቱን በማስታውስ የነበረውን የነጻነት ትግል ሁኔታ አስረድተዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም የአድዋ ድል የሀገራችንን የግዛት አንድነት ያስጠበቅንበት፣ በመላው አለም ላይ የነበሩ ጥቁር ህዝቦች ክብር ያገኙበት፣ የኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ስርዓቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መሠረት የተጣለበት እንዲሁም በቅኝ ገዢዎች ስር የነበሩ ጥቁር ህዝቦች የነጻነት ትግል እንዲያደርጉ መነሻ የሆነ እና በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ የተለየ ስፍራን የያዘ ክስተት መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በበኩላቸው አድዋ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ተሰባስበው በአንድነት እንዲቆሙና የገጠማቸውን ችግር በጋራ እንዲፈቱ ማድረግ ያስቻለ በመሆኑ ከዚህም ሁልጊዜም በአንድነት በመቆም ሀገራዊ ፈተናዎችን ማለፍ መቻልን ትውልዱ ተረድቶ ለተግባራዊነቱ መነሳት እንደሚገባው አውስተዋል፡፡

የቀረበውን የውይይት ሰነድ ተከትሎም አሁን ያለው ትውልድ ከአድዋ ድል ምን ሊማር ይገባል በሚል በተደረገ ውይይት ላይ በርካታ ሀሳብና አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን በዚህም የአሁኑ ትውልድ ከአባቶቹ የአድዋ ድል ብልሀትን፣ መተባበርንና መተጋገዝን ተምሮ በዚያው ልክ ሊተገብረው እንደሚያስፈልግ የተጠቀሰ ሲሆን በአጠቃላይ የአድዋ ድል ከተከሰተበት ወቅት በተለየ መጪው ጊዜ መልካም ሁኔታዎች የሚፈጠሩበት ሊሆን ስለሚችል በዚያው መጠን ዜጎች ማንኛውንም አጋጣሚ በመጠቀም የሚችሉትን አስተዋፅኦ በማበርከት የአድዋን የድል መንፈስ ማፅናት የሚጠበቅባቸው መሆኑ ተመላክቶ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡

Tagged Under: National Unity
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች