ፍትሕ ሚኒስቴርና የፌዴራል ፖሊስ በጋራ በመሆን ከህዝበ ውሳኔ ጋር ተያይዞ በወላይታ ዞን በተደረገው ምርጫ የህግ ጥሰቶችን ፈፅመዋል ተብለው ከተለዩት136 ተጠርጣሪዎች 93 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገለጹ

Ministry of Justice and Federal Police Announce Arrest of 93 Suspects for Election Offences in Wolaita Zone Referendum

ከደቡብ ክልል አንዱ በሆነው በወላይታ ዞን በተደረገው የሕዝበ ውሳኔ ምርጫና በመራጮች ምዝገባ ሂደት የምርጫ ሕግ ጥሰቶች ፈጽመዋል ተብለው ከተለዩት136 ተጠርጣሪዎች 93ቱ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑ ተገለጸ፡፡

መግለጫውን የሰጡት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ፈቃዱ ፀጋ እና በፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ የወንጀል ምርመራና ኦፕሬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሊሳ አብዲሳ ናቸው፡፡

በመግለጨውም ክቡር አቶ ፈቃዱ ፀጋ እንደገለጹት ለውጡን ተከትሎ እንደ አገር ከተደራጁት ተቋሞች አንዱ ምርጫ ቦርድ ሲሆን ተቋሙ በአዲስ ሕግ ተቋማዊ አደረጃጀቱን በአዲስ አመራር ከመመደብ ጀምሮ ነፃ፣ ገለልተኛና ተዓማኒ የሆኑ ምርጫዎችን እንዲያካሄድ ተቋቁሟል፡፡

ይህንንም ተከትሎ 6ኛ ሀገራዊ ምርጫን ጨምሮ የሲዳማ ክልልና የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን የተሳኩ ነፃና ገለልተኛ የሆኑ ምርጫዎችን ማካሄድ መቻሉን ያወሱት ሚኒስትር ዴኤታው የፌዴሬሸን ምክር ቤት የደቡብ ኢትዮጵያ አዲስ ክልል ምስረታን በተመለከተ ህዝቦች በህዝበ-ውሳኔ እንዲያረጋግጡ በጠየቀው መሠረት በ6 የደቡብ ክልል ዞኖች እና በ5 ወረዳዎች ላይ ህዝበ-ውሳኔ እንዲካሄድ፣ የመራጮች ምዝገባ እንዲደረግ እንዲሁም ህዝበ-ውሳኔ የሚሰጥበትን ቀን በመወሰን ወደ ስራ የተገባ መሆኑን በመግለጽ በሂደቱም 2 ጊዜ ወንጀል የገጠመ መሆኑን ጥቆማ ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴርና ለፌደራል ፖሊስ መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ክቡር አቶ ፍቃዱ ገለጻ በምርጫ ምዝገባ ሂደት በወላይታ ዞን አረካ ምርጫ ማዕከል 5 የምርጫ ጣቢያዎች፣ ሶዶ ዞን 3 የምርጫ ጣቢያዎች እንዲሁም በጎፋ ዞን ሳውላ ምርጫ ጣቢያ የገጠሙ የምርጫ አመዘጋገብ ሒደት እንከኖች በመገለጻቸው የምርጫ ቡድን ተደራጅቶ ምርመራ ተካሂዷል፡፡ ክቡር ሚኒስትር ዴዔታው አያይዘውም በሒደቱም 21 ምስክሮችን በመቀበል 38 ተጠርጣሪዎች ተለይተዋል ያሉ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በወላይታ ዞን 357 የምርጫ ጣቢያዎች፣ እንዲሁም በሌሎች 5 ዞኖች እና 4 ልዩ ወረዳዎች በ81 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች ዝርዝር መገለጹን ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሠረት ምርጫውን ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ ያስደረገና ሰፊውን ቦታ ምርመራ ማስቀደም አስፈላጊ ሆኖ በመገኙቱ በወላይታ ዞን የተፈፀመውን ወንጀል በቅድሚያ መመርመር የተጀመረ መሆኑን ክቡር አቶ ፍቃዱ አክለዋል፤ በዚህም ሂደት 2 ቡድኖች ተደራጅተው አንደኛው አዲስ አበባ ላይ ሆኖ በምርጫ ቦርድ የሚገኙ ሰነዶችን በሙሉ በመመርመር የሚሰራ ሲሆን 7 አባላት ያሉትና ከዐቃቤ ሕግና ከፖሊስ የተውጣጣ ቡድን ሆኖ በ357 የምርጫ ጣቢያዎች መዝገቦችን በማየት፣ ፊርማዎችንና ሰነዶችን በመመርመር እያጣራ ወደ ፎረንሲክ ላቦራቶሪ የሚልክ ሲሆን 2ኛው ደግሞ በወላይታ ዞን 23 አባላት ያሉት ከዐቃቤ ሕግ፣ ከፌደራል ፖሊስና ከክልሉ የተደራጀ ቡድን ሆኖ በ357 ምርጫ ጣቢያዎች እየተዘዋወረ የምስክሮችን ቃል ሲቀበል የነበረ ቡድን መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው አያይዘውም በሒደቱም ምርጫ ቦርድ በሰጠው ጥቆማ መሠረት ፊርማዎች መመሳሰል የሚታይባቸው መሆናቸውን፣ የተወሰኑ ሰዎች ተደጋጋሚ ፊርማ መፈረማቸውንና በተወሰኑ ሰዎች ጣት ፊርማ የተከናወኑ መሆናቸውን ማረጋገጥ ተችሏል፤ ሚስጥራዊነትን በጣሰ መንገድ ወደ ሚስጥራዊ ክፍል በመግባትም ጭምር ይደረጉ የነበሩ ህገ ወጥ ድርጊቶች መኖራቸውንም በሰው ማስረጃ ተረጋግጧል፤ እንዲሁም የፊርማ መደጋግምም በተወሰኑ የምርጫ አስፈፃሚዎች ይደረጉ የነበረ ስለመሆኑ በሰው ማስረጃ ለማረጋገጥ ተችሏል፤ 451 ሰዎችን በማነጋገር ከዚያም ውስጥ 79 ሰዎች ቃላቸውን እንዲሰጡ ተደርጓል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

አክለውም 136 ሰዎች ተለይተው 93 ሰዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል ያሉ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 18 የሚሆኑት በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት የወረዳና የቀበሌ አመራሮች መሆናቸውን ያሉ ሲሆን 118ቹ ደግሞ የምርጫ አስፈፃሚ ናቸው ብለዋል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ በምርጫ አዋጁ፣ በሙስና አዋጅና በወንጀል ህጉ የሚያስጠይቁ ድርጊቶች ስለመኖራቸው ተረጋግጧል ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴዔታው ቀሪ ሂደቱ በወንጀሉ ላይ የተሳተፉ ሰዎችን መለየትና ክስ ማዘጋጀት መሆኑን አውስተዋል፡፡

የምርጫ ሒደቱ ፍጹም ገለልተኛ ያልሆነ ጣልቃ የተገባበት ዜጎቹ ህዝበ ውሳኔ ያላደረጉበት በመሆኑ ማናቸውንም በዚህ ሂደት የተሳተፉትን አካላት አስተማሪና ተገቢ የሆነ ቅጣት እንዲያገኙ እንሰራለን ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

አቶ ሙሊሳ አብዲሳ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የወንጀል ምርመራ ኦፕሬሸን ዋና መምሪያ ኃላፊ የሆኑት በበኩላቸው በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች በፍትሕ ሚኒስቴር፣ በፌዴራል ፖሊስ፣ በደቡብ ክልል ፖሊስ እና በክልሉ ዐቃቤ ሕግ በጋራ በተቋቋመው የምርመራ ቡድን መሆኑን ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም መራጮች ያልሰጡትን ድምፅ በማስመሰል ኮሮጆ መሙላት፣ ያልተመዘገቡ መራጮች እንዲካተቱ ማድረግ እና ሌሎች የምርጫ ሕግ ጥሰቶች መፈጸመቸውን ተናግረዋል፡፡

ኃላፊው አክለውም የሕግ ጥሰቶቹ ህዝቡ በህገ-መንግስቱ የተሰጠውን በራሱ የመወሰን ሥልጣን በጥቂት ግለሰቦች የማጭበርበር ድርጊት ህገ-መንግስታዊ መብቱን እንዲነፈግ አድርገዋል ብለዋል፡፡ በምርጫ ቦርድ ለዞኑ የተመደበው 2ዐ5 ሚሊዮን ብር በጀትም ለከፍተኛ ጉዳት መዳረጉንም ጠቁመዋል፡፡

Tagged Under: Attorney General • Criminal Investigation • election • election fraud • federal • Federal police • Fraud • Government Officials • Human Rights Violations • Offences • peoples' • Police • public prosecutor • referendum • region • self-determination • southern • vote • zone
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች