ፍትህ ሚኒስቴር እና የኢትየጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በጋራ ሊሰሩባቸዉ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ

Ministry of Justice and Ethiopian Human Rights Commission Discuss Areas of Joint Cooperation

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር እና የኢትየጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በቀጣይ በጋራ ሊሰሩባቸዉ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በዛሬው ዕለት ሰፋ ያለ ዉይይት አድርገዋል፡፡

በዉይይቱም በተለይም በሽግግር ፍትሕ ትግበራ ሂደት፣በሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብት አገራዊ ሪፖርት (ዩፒአር) ዝግጅት እና ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ዙሪያ በፍትሕ ሚኒስቴር የተከናወኑ እና እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች ቀርበው ሁለቱ ተቋማት በጋራ ሊሰሩባቸዉ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ዉይይት ተካሂዷል፡፡

በዚህ ወቅት የፍትሕ ሚኒስትር ክብርት ወ/ሮ ሐና አርአያስላሴ እንደገለፁት ፍትሕ ሚኒስቴርና የኢትየጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጋራ የሚሰሩባቸዉን ጉዳዮችን በመለየት በቀጣይ ግንኙነታቸዉን አጠናክረዉ እንደሚቀጥሉ በመግለፅ፣ ፍትሕ ሚኒስቴር የሰብዓዊ መብትን በተመለከተ ከሚያከናዉናቸዉ ተግባራት ዉስጥ በዋናነት የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሃ ግብር መከታተል፣የታራሚዎች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ክትትል፣ሰብዓዊ መብትን በተመለከተ የንቃተ ሕግ ስራዎችን መሥራት እና ሌሎች ተግባራት እንዳሉት አንስተዋል፡፡

በመሆኑም እነዚህ ተግባራት እንዳሉ ሆነዉ በቀጣይ ከኮሚሽኑ ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችሉ በተለይም ከሽግግር ፍትሕ የትግበራ ሂደት፣ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሪፖርት ዝግጅት ፣ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት እና በሌሎች የሰብዓዊ መብት ጋር ግንኙነት ባላቸዉ ተግባራት አብሮ ለመሥራት የጋራ ስራዎችን ግልፅ በሆነ መልኩ በማስቀመጥ ግንኙነቱን ቋሚና ቀጣይነት ያለዉ እንዲሁም ተግባራዊ የሚሆን በማድረግ በጋራና በቅንጅት በመሥራት ዉጤታማ በሆነ መልኩ መተግበር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የኢትየጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ክቡር አቶ ብርሃኑ አዴሎ በበኩላቸዉ ኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብት ተግባራትን በተመለከተ ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር እያደረጋቸዉ ያሉ ዉይይቶች ተስፋ ሰጭ መሆናቸዉን አንስተዉ በቀጣይ በሚኖሩ ተግባራት ቴክኒካል ቡድን በማዋቀር ጭምር ተገቢዉን ድጋፍ በማድረግ አብረን እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።

አያይዘዉም ከሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራ፣ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሪፖርት ዝግጅት እና ከነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ጋር ተያይዘዉ በተነሱ ስራዎች ዙሪያ በተለይም በሚደረጉ ህዝባዊ ዉይይቶችን በሚመለከቱ ስራዎች ላይ ኮሚሽኑ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በትብብር መሥራት እንደሚችል አመላክተዋል።

በቀጣይ ሁለቱ ተቋማት በእነዚህና ሌሎች በጋራ መሥራት በሚችሉባቸው ተግባራት ዙሪያ የጋራ ስምምነት ሰነድ በማዘጋጀት ወደ ስራ እንደሚገቡ ተጠቁሟል፡፡

Tagged Under: Cooperation Human Rights Legal Aid transitional justice
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች