ስለ ዓለምአቀፍ ህግ ምን ያህል ያውቃሉ?

How Much Do You Know About International Law?

በዓለም ላይ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት 193 አባላት እና 2 አባል ያልሆኑ ሀገራት በድምሩ 195 የሚሆኑ ሀገራት ያሉ ሲሆን እነዚህ ሀገራት የውስጥ ጉዳያቸውን የሚያስተዳድሩበት ሀገራዊ ሕግ አላቸው። ነገር ግን የአንድ አገር ጉዳይ በአገር ውስጥ ጥረት ብቻ ሊሟላ አይችልም፡፡ ስለዚህ ሁሉም አገራት በሚያገናኟቸው ጉዳዮች ላይ በትብብር ይሰራሉ። በተለይም በዚህ ሉላዊነት በነገሰበት ዓለም ሀገራት በፈጠሩት ትስስር ወደ መንደርነት መጥተዋል፡፡ ለትስስሩ ውጤታማነት ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሁነኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል። ይህ ትስስር የትኛውንም በጎም ሆነ መጥፎ ነገር በቀላሉ ከአንዱ የዓለም ጫፍ ወደ ሌላው ጫፍ እንዲስፋፋ አድርል፡፡ ከወንጀል መከላከል አንጻር ብናየው ወንጀለኞች የወንጀል ሀሳባቸውን በአንዱ አገር አስበው በሌላ አገራት በአካል መገኘት ሳያስፈልጋቸው እንዲፈጽሙ አስችሎአቸዋል፡፡ ከዚህ አንጻር ድምበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን መከላከሉም አለማቀፍ ትብብር የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ አገራት በየትኛውም ጉዳይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ግንኙነት ለማድረግ ይገደዳሉ፡፡ ከሕግ አሠራር አንጻር ብዙ የጋራ ጥረት እና ትብብር የሚጠይቁ ጉዳዮች አሉ፡፡ አለምአቀፍ ሕግ ሀገራት እርስ በርስ የሚኖራቸውን ይሄንኑ ግንኙነት የሚገዛ ሕግ ነው፡፡ በአለምአቀፍ ሕግ ዋና ተገዚዎች ሀገራት ሲሆኑ፣ እንደየሁኔታው አለምአቀፍ ድርጅቶች እና ግልሰቦችም በዚሁ ሕግ የሚመሩበት ሁኔታ አለ፡፡

የዓለም አቀፍ ሕግ ምንጮች

በአለምአቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት ማቋቋሚያ ስምምነት (ICJ statute) አንቀጽ 38 መሠረት ዓለም ዓቀፍ ሕግ የሚመነጨው በዋናነት:-

⎫ ከአለምአቀፍ ስምምነቶች፣

⎫ ከአለምአቀፍ ልማዳዊ ሕግጋት፣

⎫ ጠቅላላ የሕግ መርሆች፣ ሲሆኑ

በተጨማሪም

⎫ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች እና

⎫ በአለማቀፍ ሕግ የታወቁ ምሁራን ከሚያሳትሙት ጽሁፍ የሚገኝ አስተምህሮት (teachings of the most highly qualified publicists of the various nations) በማስረጃነት የሚታዩ ናቸው፡፡

የአለምአቀፍ ስምምነት (Treaty Laws) ምን እንደሆነ ያውቃሉ?

አለምአቀፍ ስምምነት ሲባል ሁለት እና ከሁለት በላይ የሆኑ ሀገራት እርስ በር ለሚኖራቸው ግንኙነት እንዲመራበት አስበው የሚፈራረሙት የሕግ አይነት ነው፡፡ የ1969 የቬና አለምአቀፍ የስምምነት ሕግ አንቀጽ 2(1)(ሀ) አለምአቀፍ ስምምነትን ሲገልጸው ‘an international agreement concluded between States in written form….” ሲል ያስቀምጣል፡፡ ትርጉም በመግቢያው ካስቀመጥነው ጋር የሚመሳሰል ሲሆን ይህ ስምምነት የሚፈረምበት የራሱ የሆነ ፎርማሊቲ አለው፡። እርሱም በጽሁፍ መሆን አለበት፡፡ በሀገራችን በአለምአቀፍ ስምምነት መዋዋያ እና ማጽደቂያ አዋጅ ቁጥር 1024/2009 አንቀጽ 2(7) መሠረት አለምአቀፍ ስምምነት ሀገራችን ኢትዮጵያ ከሌላ ሀገር ጋር ወይም ከሌሎች ሀገራት ጋር ወይም ከአለምአቀፍ ድርጅቶች ጋር የምትፈራረመው ስምምነት እንደሆነ ደንግጓል፡፡ ይህ ትርጉም ከቬናው ስምምነት ትርጉም ጋር ተቀራራቢ ሲሆን አለምአቀፍ ድርጅቶች ጋር የሚደረገውንም ስምምነት አካቶ ይገኛል፡፡ የቬናው ስምምነት ተፈፃሚነት ወሰን በሀገራት መካከል የሚደረጉ ስምምነቶች ላይ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን ዓለምአቀፍ ስምምነቶች በሀገራት መካከል ከሚደረጉ ስምምነቶች በተጨማሪ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች የሚያደርጓቸውን ስምምነቶችንም የሚያካትት መሆኑ ነው፡፡ አለምአቀፍ የስምምነት ሕግ ሌሎች አለምአቀፍ ሕግጋትን በመከተል መፈረም ያለበት ሲሆን በተለያዩ መጠሪያዎች በተለዋዋጭነት ይጠራል፡፡ እነሱም ስምምነት (agreements)፣ ቃልኪዳን (conventions)፣ ፕሮቶኮል (protocols) ወይም ኮቬናንት (covenants) እየተባለ ሊጠራ ይችላል፡፡ ስምምነቱ አለምአቀፍ ሕግ የሚሆነው ተፈራራሚ ሀገራት ሉአላዊ ሀገራት ከሆኑ ብቻ ነው። ይህ ማለት በአንድ ሀገር ውስጥ ያሉ ክልሎች ወይም የአካባቢዎች አስተዳደር አካላት አለምአቀፍ የስምምነት ውል ሊዋዋሉ አይችሉም ማለት ነው። አንድ ሉዓላዊ አገር ከሌላ ሉዓላዊ አገር የክልል አስተዳደር ጋር ስምምነት ማድረግም በአለምአቀፍ ሕግ መሠረት ህጋዊ ውጤት የማይኖረው ነው፡፡ ዓለምአቀፍ ስምምነቶች በተለያዩ መስፈርቶች የተለያዩ ክፍፍሎች ቢኖራቸውም ከአባል ሀገራት ብዛት አንፃር በሁለት የሚከፈሉ ሲሆን እነርሱም ባለሁለት ወገን ስምምነቶች (bilateral treaty) እና ባለብዙ ወገን ስምምነቶች (Multilateral treaty) ተብለው ሊከፈሉ ይችላል፡፡ ትርጉሙም ከቃሉ መረዳት እንደሚቻለው የፈራሚ አገራትን ብዛት መሠረት ያደረገ ሲሆን ሁለት ሀገራት ብቻ እርስ በርስ የሚያድጉት ስምምነት ባለሁለት ወገን ስምምነት ይባላል፡፡ የፈራሚ አገራት ብዛት ከሁለት በላይ ከሆነ ባለብዙ ወገን ስምምነት ይባላል፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገር ሱዳን ጋር ወንጀለኞችን አሳልፎ ለመስጠት የምታደርገው ስምምነት ባለ ሁለት ወገን ስምምነት ሲባል የኢጋድ አባል ሀገራት ፍርደኛን ለማስተላለፍ የሚያደርጉት የጋራ ስምምነት ባለብዙ ወገን ስምምነት ይባላል፡፡ ምክንያቱም የኢጋድ አባል ሀገራት ከሁለት የበለጡ ስለሆኑ ነው፡፡ በተጨማሪም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሕግ ማዕቀፍን፣ የአፍሪካ ህብረት እና ሌሎች አህጉራዊ ወይም ቀጠናዊ ባለብዙ ወገን ስምምነቶችን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

ሀገራችን የምትፈርማቸው አለምአቀፍ ስምምነቶች የሚ ጸድቅባቸውን ሂደት ያውቃሉ?

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ-መንግሥት አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 4 እና አንቀጽ 55 ንዑስ አንቀጽ 12 መሠረት አንድ አለምአቀፍ ስምምነት የሀገራችን ሕግ አካል እንዲሆን መጽደቅ እንዳለበት ይደንግጋል፡፡ ይህንኑ የህገመንግስቱን ድንጋጌ ለማስፈጸም የወጣው የአለምአቀፍ ስምምነቶች መዋዋያ እና ማጽደቂያ አዋጅ ቁጥር 1024/2009 አንቀጽ 6(1) መሠረት አለምአቀፍ ስምምነትን የመደራደር እና የመዋዋል ሥልጣን የጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንደሆነ ደንግጓል፡፡ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት ሌሎች የመንግሥት ባለስልጣናት መሰል ስምምነቶችን መደራደር እና መዋዋል የሚችሉት ባለሙሉ ሥልጣን ውክልና ከተሰጣቸው ብቻ ነው፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 4 መሠረት የድርድር ሀሳቡን የሚያቀርበው የመንግሥት አካል ባለድርሻ አካላትን በማማከር አስተያየታቸውን ማካተት እና ስምምነቱ አገራችን ላይ የሚጥላቸውን ግዴታዎች ብሎም የሚያስገኘውን ጥቅም በተመለከተ ማብራሪያ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ጽ/ቤት ማቅረብ አለበት፡፡ በዚሁ ሕግ መሠረት ስምምነቱ አዲስ ሕግ እንዲወጣ እና ነባር ሕግ እንዲሻር የሚያደርግ ከሆነ የኢ.ፌ.ድ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር አስተያየት መጠየቅ አለበት፡፡ አለምአቀፍ ስምምነቱ ከድርድር እና መዋዋል በኋላ በህገመንግስቱ መሠረት በሚኒስትሮች ምክር ቤት እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጽደቅ እንዲችል የግድ መቅረብ አለበት፡፡ ለዚህም በአዋጅ ቁጥር 1024/09 አንቀጽ 10 መሠረት ድርድሩን ያደረገው የመንግሥት አካል የስምምነቱን ቅጅ፣ የይዘቱን ማብራሪያ አጭር መግለጫ እና ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅ በማዘጋጀት በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማkkሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6 ንዑስ አንቀጽ 5(ሐ) መሠረት ከፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ አስተያየት ተሰጥቶበት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ይቀርባል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤትም ስምምነቱ እዲጸድቅ ሲወስን ከላይ የተገለጹ ስምምነቱ እና ማብራሪያው እንዲሁም ረቂቁን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረብ አለበት፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 11 መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ስምምነቱን ከተቀበለው የማጽደቂያ አዋጅ ያወጣል።

ሀገራት በአንድ ስምምነት ላይ የተወሰኑ ክፍሎች ላይ ተዓቅቦ (reservation) ማድረግ የሚችሉ ሲሆን በማፅደቅ ሂደቱ ይህ ካለ ማጽደቂያው ይሄንኑ ማካተት አለበት፡፡ በዚህ ሂደት ያለፈ አለምአቀፍ ስምምነት የሀገራችን ሕግ አካል ይሆናል፡፡

ልማዳዊ አለምአቀፍ ሕግ ምንድን ነው?

ልማዳዊ አለምአቀፍ ሕግጋት የሚባሉት ከመደበኛው እና ከተፃፈው ስምምነት ወይም ቃልኪዳኖች የሚመነጩ ሳይሆን ከሀገራት አለምአቀፍ ተግባርና ልማድ የሚመነጩ ሕግጋት ሆነው ሀገራት በተደጋጋሚነት እና በተከታታይነት ሲተገብሯቸው የቆዩ ጠቅላላ ተግባራዊ ልምዶች (general state practices) እና ሀገራቱ እነዚህኑ እየተገበሯቸው ያሉት ልምዶች እንደ አስገዳጅ ሕግ ተቀብለዋቸው (opinio juris) ከሆነ እንደ ልማዳዊ አለምአቀፍ ሕግ የሚወሰዱ ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት በሀገራት አለምአቀፍ ግንኙነት ውስጥ አንድን ግዴታ ወይም መብትን በመቀበል በተደጋጋሚ ተመሳሳይ አቋምና ተግባር ካለ ወደፊት በዚህ ጉዳይ የዚህ ሀገር መብት ወይም ግዴታ ምንድነው ሲባል ይህው ልማድ እንደሆነ ይወሰዳል ማለት ነው፡፡ ይህ የሀገር አቋምና ተግባር በሀገር መሪ፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ በሚመለከተው ሚኒስተር፣ አምባሳደር ንግግርና ተግባር ወይም ከሀገሪቱ ተቋማት ወይም ፍርድ ቤት ሊወሰድ ይችላል፡፡ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ሀገራትን ወክለው በአለምአቀፍ መድረክ በወከላቸው ሀገር ስም የሚያደርጓቸው ንግግሮች፣ የሚይዝዋቸው አቋሞች ተደጋግመው እና እንደ አለምአቀፍ ግዴታ ሲወሰዱ ልማዳዊ አለምአቀፍ ሕግ ሆነው ወደፊት በሚነሱ መሰል ጉዳዮች ላይም አስገዳጅ ተፈታሚነት ይኖራቸዋል፡፡ ለምሳሌ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን (ዓባይ) በፍትሀዊነት መጠቀም እና ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያለን አለማቀፍ ድንበር ውዝግብ በተመለከተ ሀገራችን በተወካዮች በኩል በአለምአቀፍ መድረክ የምትይዘው አቋም እንደ ልማዳዊ ሕግ እያደገ ስለሚሄድ የሀገሪቱን ዘላቂ ጥቅም ያስጠበቀ ወጥነት ያለው እና የማይናወጽ አቋም ይዞ ጉዳዩን መከታተል ያስፈልጋል፡፡

በስምምነት ሕግ ከተጻፉ ጉዳዮች የተወሰኑ ጉዳዮች በአለምአቀፍ ደረጃ ሙሉ ስምምነት በሚያስብል ደረጃ ስምምነት የተደረሰባቸው እንደ አስገዳጅ ሕግ ሀገራት በራሳቸው ፍላጎት የሚተገብሯቸው ሲሆን እነዚህ ጉዳዮች የሚታዩበት አግባብ ከፍ ወደሚል ልማዳዊ አለምአቀፍ ሕግነት አድጓል፡፡ ለምሳሌ በተባበሩት መንግስታት ስምምነቶች በክልከላነት የተደነገጉ ሰውን ማሰቃየት፣ እንደ ሰው እውቅና አለመስጠት እና በባርነት አለመያዝ፣ ያለፍርድ ቤት ውሳኔ አለመገደል፣ በአራቱ የጄኔቫ ስምምነቶች የተደነገጉ የጦርነት ወይም የሰብዓዊነት ሕግጋት ውስጥ የተካተቱ ልዩ ልዩ ጉዳዮች ወደ ልማዳዊ አለምአቀፍ ሕግነት ደረጃ ያደጉ ልምዶች (አለምአቀፍ ግዴታዎች) ተደርገው ይወሰዳሉ (jus cogens)፡፡ እነዚህ ጉዳዮች የእኛም ሀገር ሕግ አካል ሲሆኑ በኢ.ፌ.ድ.ሪ. ህገመንግሥት፣ የወንጀል ሕግ እና ሌሎች ሕግጋቶቻችን ውስጥ በስፋት የተደነገጉ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ስለ ጠቅላላ የሕግ መርሆች

ጠቅላላ የሕግ መርሆች የሚባሉት በዲሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ በሂደት የዳበሩ እና በየሀገራቱ የሕግ ሥርዓት ተግባራዊ የሚደረጉ ሆነው በዚህም አለምአቀፍ ተቀባይነት ያገኙ መርሆች ናቸው፡፡ እነዚህ መርሆች በአለምአቀፍ ግንኙነት እና ክርክር አፈታት ሂደት ላይ ተግባራዊ ሊደረጉ የሚችሉ የሕግ መርሆች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ውል የገባ በውሉ የተጣለበትን ግዴታ እንዲያከብር “ቃሉ ማሰሪያው ነው” (Pacta sunt servanda)፣ በአገራት ግንኙነት ሂደት የቅን ልቦናን መርህ (good faith) መከተል የሚሉ እና መሰል መርሆች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ መርሆቹ በአንድ ሀገር ብቻ ሳይሆን ስፋት ባለው መልኩ በተለያዩ ሀገራት የሕግ ሥርዓት የዳበሩ መርሆዎች መሆን አለባቸው፡፡

የትኞቹ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች ናቸው በአለምአቀፍ ሕግ ምንጭነት የሚወሰዱት?

በአለምአቀፍ ሕግ የፍርድ ቤቶች ውሳኔ አዲስ ለሚታዩ ጉዳዮች እንደ መርህ መጠቀም የማይፈቀድ መሆኑን ከአለምአቀፍ የፍትሕ ፍርድ ቤት ማቋቋሚያ ስምምነት (ICJ statute) አንቀጽ 59 መረዳት ይቻላል፡፡ በዚሁ ስምምነት መሠረት የውሳኔው ተፈጻሚነት በተከራካሪ ወጎኖች ላይ ብቻ መሆኑን ደንግጓል፡፡ ነገር ግን ከአለምአቀፍ የፍትሕ ፍርድ ቤት (ICJ) እና ሌሎች አለምአቀፍ ፍርድ ቤቶች ተፈጻሚነት ያለውን አለምአቀፍ ሕግ ለመለየት የራሳቸውን ያለፈ ውሳኔ ተመልሰው የሚያዩበት አሠራር ያለ በመሆኑ አለምአቀፍ ሕግ ምንጭነት የፍርድ ቤት ውሳኔን ማግለል የሚቻል አይደለም፡፡ በተለይም ከዚህ ቀደም በተሰጠ ውሳኔ የአንድ አለምአቀፍ ስምምነት ወይም የአንድ ግዴታ መኖር አለመኖር በምን መልኩ እንደተተረጎመ በማጣቀስ የአለምአቀፍ ሕግን ለመለየት ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ የየትኛው ፍርድ ቤት? የአለምአቀፉ ወይስ ሀገራዊ ፍርድ ቤት ውሳኔ? ለሚለው ጥያቄ ሁለቱም አስፈላጊ ናቸው፡፡ አለምአቀፉ ፍርድ ቤት ከላይ ባነሳነው መልኩ የሚተገበር ሲሆን ሀገራዊ ፍርድ ቤት ውሳኔም ሀገራት አንድን አለምአቀፍ ግዴታ የሚጥልን ጉዳይ ከዚህ በፊት የወሰኑበትን አግባብ በማየት ግዴታው በሀገራቱ የሕግ ሥርዓት ያለ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ወይም ሀገራቱ ጉዳዩን ልማዳዊ አለምአቀፍ ሕግ ማድረጋቸውን ለማረጋገጥ በአስረጅነት ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል። በዚህ አግባብ ውሳኔዎች የአለምአቀፍ ሕግ ምንጭ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡

በአለማቀፍ ሕግ የታወቁ ምሁራን ከሚያሳትሙት ጽሁፍ የሚገኙ አስተምህሮቶች እና ሌሎች በህጉ በግልፅ ያልተገለጹ ጉዳዮች ላይ ያሉ ትርጓሜዎችና ትንታኔዎች በማስረጃነት የሚታዩ መሰል ጉዳዮች እንደ ሁኔታው የሚያስፈልጉ እና በሁለተኛ ደረጃ በአለምአቀፍ ሕግ ምንጭነት የሚገለጹ ናቸው።

የአለምአቀፍ ሕግን ተፈጻሚነት ወሰን ያውቁ ኖሯል?

ዓለምአቀፍ ሕግ እንደ የህጉ ምንጭ የአፈጻጸሙ ወሰንም የሚወሰን ነው፡፡ ከስምምነት የሚመነጭ አለምአቀፍ ሕግ ተፈጻሚነቱ በፈራሚ ሀገራት ላይ ብቻ ሲሆን ፈርመውም በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ተዓቅቦ ያሰሙ ፈራሚ ሀገራት በታቀቡበት ጉዳይ ላይ እንዲፈጸምባቸው አይገደዱም። ከልማዳዊ አለምአቀፍ ሕግ ጋር በተገናኘም ከላይ እንዳነሳነው የተፈጻሚነት ወሰኑ የሚታወቀው የሀገራትን ጠቅላላ ልምድ እና እንደ ሕግ ግዴታ ጉዳዩን መቀበላቸው ነው። በእያንዳንዱ ጉዳይ ከሀገር ሀገር ይለያያል፡፡ ነገር ግን ቀደም ሲል እንዳነሳነው አንዳንድ አለምአቀፍ ግዴታዎች ጠቅላላ ግንዛቤ ተፈጥሮ በሁሉም ሀገራት እንደ ግዴታ የሚፈጸሙበት ሁኔታ በልማድ ሂደት ስለተፈጠረ እንደነዚህ አይነቶቹ አለምአቀፍ ግዴታዎች የተፈጻሚነታቸውን ወሰን በአለምአቀፍ ደረጃ ያደርገዋል፡፡

በጥቅሉ አለምአቀፍ ሕግ የሉዓላዊ ሀገራት ግንኙነት የሚመራበትን የሕግ ማዕቀፍ የሚደነግግ ሕግ ሲሆን ተፈጻሚነቱም እንደ ህጉ ባህሪ በፈራሚ ሀገራት፣ በአባል ሀገራት፣ እና እያንዳንዱ ሀገራት ላይ ነው፡፡ ሀገራችንም ከዚህ አንጻር ያላት አለምአቀፍ ግንኙነት በዚሁ ሕግ አግባብ የሚመራ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡

እናመሰግናለን!

በዮሃንስ ግርማከንቃተ ሕግ፣ ትምህርት እና ሥልጠና ዳ/ት

Tagged Under: customary law • International law • Legal Education • treaties
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች