የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ እና የዘርፉ መካከለኛ አመራሮች በተገኙበት ሐምሌ 08 ቀን 2017 ዓ.ም የዘርፉን የ2017 በጀት ዓመት የአፈጻጸም ሪፖርት እና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ዉይይት ተደርጓል፡፡
ውይይቱን በንግግር የከፈቱት ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ በ2017 በጀት ዓመት በዘርፉ በርካታ አገራዊ ፋይዳ ያላቸው ተግባራት ታቅደው የተከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በመቀጠልም የሕዝብና የመንግሥት ፍትሐብሔራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ፤ የሕግ ጥናቶችን ከማከናወን፤ ሕጎችን ከማርቀቅ እና ማጠቃለል፤ ከወንጀል መከላከል ስትራቴጂ አተገባበር ክትትል፣ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝን ክትትል ከማድረግ፤ በሕግ ጉዳዮች ዓለም ዓቀፍ ትብብር ከማሳደግ፤ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ከመከላከልና መቆጣጠር፤ የፌደራል ጠበቆችን ከማስተዳደር፣ የፌደራል መንግስቱ ሕጎች ወጥ በሆነ አግባብ መተግበራቸውን ከማረጋገጥ እና ከሌሎች የዘርፉ ኃላፊነቶች አንጻር በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ ተግባራትና የተገኙ ዋና ዋና ስኬቶች፤ በአፈጻጸም ወቅት ያጋጠሙ ችግሮችንና የተወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በመቀጠልም የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት የዘርፍ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፣ ግብዓት ተሰብስቧል፡፡ በውይይቱም ማጠቃለያ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ በ2017 በጀት ዓመት የነበሩ ጠንካራ አፈጻጸሞችን በማስቀጠል እና የታዩ ክፍተቶችን በመሙላት የአዲሱን በጀት ዓመት አፈጻጸም የተሻለ ለማድረግ በሂደት ላይ ያሉ አገራዊ ስራዎችን ጨምሮ በዚህ በጀት ዓመት በዕቅድ የተያዙ ስራዎች ላይ በተሻለ ተነሳሽነትና ትኩረት መሰራት እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡