መካከለኛ አመራሮች ስትራቴጂያዊ እቅድ በማዘጋጀት እና በማስፈፀም ረገድ ያላቸዉ ኃላፊነት ከፍተኛ በመሆኑ ይህንኑ ኃላፊነት በብቃት ይወጡ ዘንድ አቅም ማጎልበት ተገቢ ነዉ፡፡ ከዚህ አኳያ የኢፌዴሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ለመካከለኛ አመራር እና ሠራተኞች በተለያዩ ርእሶች አቅም ማሳደጊያ ስልጣና በማቀድ እንዲሰለጥኑ እያደረገ ይገኛል፡፡
የስትራቴጂክ አመራር ፣የስትራቴጂክ ዕቅድ እና የለውጥ አመራርን አስመልክቶ ለፍትሕ ሚኒስቴር መካከለኛ አመራሮች ከሐምሌ 25-27/2017 ዓ.ም የሚቆይ ሥልጠና በተቋሙ የንቃተ ሕግ፣ ትምህርት እና ሥልጠና ዳይሬክቶሬስ አዘጋጅነት በአውሮፓ ህብረት ድጋፍ በአዳማ ከተማ እየተሰጠ ይገኛል፡፡
የሥልጠና መድረኩን በንግግር የከፈቱት በፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ኤርሚስ የማነብርሃን (ዶ/ር) የተቋሙ አምስት ዓመት የስትራቴጂክ ዕቅድ እየተዘጋጀ መሆኑን አንስተው በዚህም የተቋሙ አመራሮች የእቅዱ ባለቤት በመሆናቸው በዕቅዱ ዙሪያ ልምምድ የሚያደረጉበት ሥልጠና መሆኑን አውስተዋል፡፡
የተቋሙ የስትራቴጂክ አመራር߹የስትራቴጂክ ዕቅድ እና የለውጥ አመራር ፕሮጀክትን አስመልክቶ በአማካሪ ድርጅቶች ጥናት በማስጠናት የጥናቱ ግኝትን አስመልክቶ ሥልጠና መስጠት አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ለሥልጠና አስፈላጊ የሆኑ ሞጁሎች ተዘጋጅተው ከዚህ በፊት ለዐቃቤ ሕግና አስተዳደር ሠራተኛ ቡድን መሪዎች እንዲሁም የፅህፈት ቤት ኃላፊዎች ሁለት ዙር ሥልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
የሥልጠናው ዓላማ የቀጣዩን አምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ እያዘጋጁ ላሉ አካላት ግብዓት መስጠትና የዕቅድ ልምምድ ዝግጅት ማድረግ መሆኑን አንስተው የተቋሙ ስትራቴጂክ ዕቅድ የተሟላ እንዲሆን የማይተካ ሚናቸውን እንዲወጡ ያሳሰቡት ሚኒስቴር ዴኤታው እየተዘጋጀ ያለው ስትራቴጂክ ዕቅድ ከቀድሞው ለየት የሚያደርገው ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ እየተዘጋጀ መሆኑ ነው ብለዋል።
ዛሬ የተጀመረው ይህ ሶስተኛ ዙር ሥልጠና በተቋሙ ከፍተኛውን የሥራ ድርሻ እየተወጡ ላሉ መካከለኛ አማራሮች እንደሆነ የገለፁት ሚኒስትር ዴኤታው ሥልጠናው ለተቋሙ ስትራቴጂክ ዕቅድ አስፈላጊ በመሆኑ ሰልጣኞች በባለቤትነት አሰልጣኞች ደግሞ ሥልጠናውን በማስተባበር በኩል የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡